አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አርሶ አደሩ በዝናብ ወቅት ሳይገደብ የግብርና ሥራውን ዓመቱን ሙሉ ማከናወን እንዲችል በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)።
በምስራቅ ጉራጌ ዞን ደቡብ ሶዶ ወረዳ በክልሉ ግብርና ቢሮ ከ56 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የሲቢስቶ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክት ተመርቋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አካባቢው ከመደበኛ የሰብል ልማት በተጨማሪ ልዩ ልዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የሚታወቅ ነው።
በክልሉ የመስኖ ተቋማትን በማስፋት ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ በዘርፉ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ስሩር በበኩላቸው÷ መንግሥት ሕዝቡን ከድህነት በማውጣት ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት እሳቤዎችን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሲቢስቶ የመስኖ ፕሮጀክትም አርሶ አደሩ ትርፍ አምራች እንዲሆንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የመስኖ ፕሮጀክቱ 175 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው ሲሆን÷ 700 አባወራዎችን ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

