አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከለውጡ በኋላ የአፋር ሕዝብ ከአጋርነት ወደ ባለቤትነት ተሸጋግሯል አሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ።
በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ፣ በዱብቲና አካባቢው ለብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የዴሞክራሲና እኩልነት ጥያቄ በአሁኑ ወቅት ምላሽ እያገኘ ነው።
በዚህም በፖለቲካና አስተዳደር ጉዳይ የአፋር ሕዝብ ከለውጡ በኋላ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት፣ የእኩልነትና የባለቤትነት መብቱ በሙሉነት ተረጋግጧል ብለዋል።
እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን በተሰራው ስራ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የኮራ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገንብቶ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል።
የክልሉ ገቢ ዕድገት በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 790 ሚሊየን ብር ወደ 8 ቢሊየን ብር ማደጉን ገልጸው÷ የእርሻ ልማት ሽፋን ከ53 ሺህ ሄክታር ወደ 138 ሺህ ሄክታር በማሳደግ 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉንም አብራርተዋል።
በክልሉ ከለውጡ በፊት የማይታወቀው የስንዴ ልማት በአሁኑ ወቅት ከ16 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በላይ በማልማት 276 ሺህ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።
በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርና በሌሎች ዘርፎችም የተሻለ ውጤት መመዝገቡን መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

