Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ መኖሩ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገሪቱ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ላይ ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ መኖሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክትትል ቡድኖች ሪፖርት አመላከተ፡፡

ቦርዱ ሥምሪት የሰጣቸው የክትትል ቡድኖች 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድባቸውን አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታን በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ የሚካሄድባቸውን አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከክልሎችና ከከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም ተጨባጭ የጸጥታ ሁኔታን ለመገምገም ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከቦርዱ የተውጣጣ የክትትል ቡድን ማሰማራቱ ይታወቃል።

የሥምሪት ቡድኑ ሪፖርቱን ለቦርዱና ለባለድርሻ አካላት ያቀረበ ሲሆን፥ በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ መኖሩን አረጋግጧል፡፡

በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች ላይ ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ ቢኖርም አሁንም ትኩረት የሚሹ ቦታዎች እንዳሉ አመልክቷል፡፡

የክትትል ቡድኑ ከፀጥታ ሁኔታ በተጨማሪ የየአካባቢዎቹ ፓርቲዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ስራዎቻቸውን በመከወን አንጻር ያለውን ሁኔታ ገምግሟል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ መድረኩ የክትትል ቡድኑ ባቀረበው ሪፖርት መሰረት ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥና የባለድርሻ አካላትን ሚና በተመለተ ለመወያየት ያለመ ነው።

በመድረኩ ስለ ጸጥታና መዋቅራዊ ተግዳሮቶች እንዲሁም መወሰድ ስላለባቸው የእርምት ርምጃዎች ውይይት መደረጉን ቦርዱ አስታውቋል፡፡

Exit mobile version