አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ትኩረቱን በሀገራዊ የስታትስቲክስ ሉዓላዊነት እና የተቀናጀ የልማት አስተዳደር ላይ ያደረገ ብሔራዊ ጉባኤ እና ኤግዚቢሽን ይካሄዳል፡፡
ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ጉባኤው “የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለሁለት ቀናት ነው የሚካሄደው።
ጉባኤው በኢትዮጵያ መረጃ የሚመራበትን፣ የሚተዳደርበትን እና ለሀገራዊ ልማትና አስተዳደር ጥቅም ላይ የሚውልበትን ሁኔታ ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከነበረው ያልተቀናጀ የመረጃ ሥርዓት በመውጣት፤ ወደተቀናጀ ዲጂታል እና ወደ ሀገር በቀል የመረጃ ሥነ ምህዳር ያደረገችውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳየት ጉባኤው ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተመላክቷል።
አንድ ዕቅድ፣ አንድ ሪፖርት፣ አንድ በጀት የሚለውን የተቀናጀ ሀገራዊ አሠራር በተቋማት መካከል ሙሉ በሙሉ ለማስፈን ጉባኤው መሠረት እንደሚጥል ነው የተገለጸው፡፡
ከጉባኤው ጎን ለጎን የሀገሪቱን የዳታ አብዮት ሽግግር እና የተከናወኑ የዲጂታል ዘመናዊነት ሥራዎችን የሚያሳይ ኤግዚቢሽንም በይፋ ይከፈታል።
በመሳፍንት ብርሌ

