Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮ ሳዑዲ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስጠበቅ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ መጠናከር አለበት – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ እና የሳዑዲ አረቢያን የጋራ ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ይበልጥ መጠናከር አለበት አሉ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሳኡዲ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ ኤልኬሬጅ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ቀጣናዊ የጋራ ፍላጎቶች ዙሪያ መክረዋል።

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ሳዑዲ የረጅም ጊዜ ግንኙነት እና የህዝብ ለህዝብ ትስስር አላቸው።

የሀገራቱን የጋራ ጥቅም ለማስጠበቅ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት መጠበቅ እና በህጋዊ መንገድ ለሚመጡ ኢትዮጵያውያን አዳዲስ የስራ እድሎችን ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ዋሊድ ኤልኬሬጅ በበኩላቸው÷ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ እና ከህዝቦቿ ጋር ያላትን የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጠው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በሕጋዊ መንገድ ወደ ሳዑዲ የሚገቡበትን ሁኔታ በመፍጠር ደህንነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሁለቱ ወገኖች በሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን የተለዋወጡ ሲሆን፤ በተለይም በቀጣናው የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለመፍታት ውይይት ብቸኛው አማራጭ ሊሆን እንደሚገባ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

Exit mobile version