Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኤሲሚላን ራሱን ለዓለም ያሳየው አንድሪያ ፒርሎ…

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጣሊያናዊው የኤሲሚላን የቀድሞ ኮከብ አንድሪያ ፒርሎ ከምንጊዜም ምርጥ የመሐል ሜዳ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡

በፈረንጆቹ 1979 በዛሬዋ ዕለት የተወለደው አንድሪያ ፒርሎ የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው በሀገሩ ክለብ ብሬሺያ ነው፡፡

ከምንጊዜም ታላላቅ የመሐል ሜዳ ተጫዋች መካከል አንዱ የሆነው ፒርሎ በእይታው፣ በፈጠራ ብቃቱ፣ በሚያቀብላቸው ኳሶች እና በፍፁም ቅጣት ምት ችሎታው ይታወቃል።

ፒርሎ ከብሬሺያ በኋላ ወደ ኢንተርሚላን ቢያቀናም መቆየት የቻለው ለሁለት የውድድር ዓመት ብቻ ነበር፡፡

በኢንተርሚላን በቆየባቸው ሁለት ዓመታት በሁሉም ወድድሮች 40 ጨዋታዎችን ብቻ ነበር ማድረግ የቻለው፡፡

የኢንተርሚላን ቆይታውን ያለምንም ዋንጫ ካጠናቀቀ በኋላ ለሬጂና እና ብሬሺያ በውሰት ውል ተጫውቶ በ2001/02 የውድድር ዓመት ኤሲሚላንን ተቀላቅሏል፡፡

አብዛኛውን የእግር ኳስ ሕይወቱን በኤሲሚላን ያሳለፈው አንድሪያ ፒርሎ በዋንጫ የታጀቡ 10 ስኬታማ ዓመታትን አሳልፏል፡፡

ፒርሎ ከኤሲሚላን ጋር የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ፣ የዓለም ክለቦች ዋንጫ፣ የአውሮፓ ሱፐር ካፕ፣ የጣሊያን ሴሪ ኤ እና የኮፓ ኢታሊያ ዋንጫዎችን ማሳካት ችሏል፡፡

የመሐል ሜዳው ኮከብ ለኤሲሚላን ባደረጋቸው 401 ጨዋታዎች 41 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡

በፈረንጆቹ 2007 በባሎንዶር የሽልማት ሥነ ሥርዓት 5ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን ሦስት ጊዜ የመጨረሻ 10 ውስጥ መግባት ችሏል፡፡

ከኤሲሚላን በኋላ ለሌላኛው የጣሊያኑ ክለብ ጁቬንቱስ የፈረመው ፒርሎ ከቡድኑ ጋር የሴሪ ኤውን ዋንጫ አራት ጊዜ ያነሳ ሲሆን በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ እስከ ፍጻሜ ተጉዟል፡፡

በጣሊያን ሴሪ ኤ በነበረው ቆይታ ሦስት ጊዜ የሴሪ ኤ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠ ሲሆን አራት ጊዜ ደግሞ የሴሪ ኤው የዓመቱ ምርጥ ስብስብ ውስጥ መካተት ችሏል፡፡

ከጁቬንቱስ በኋላ ወደ አሜሪካ በማቅናት ለኒውዮርክ ሲቲ በመጫወት በፈረንጆቹ 2017 ጫማውን መስቀሉ ይታወሳል፡፡

ሀገሩ ጣሊያንን ከፈረንጆቹ 2002 እስከ 2015 ያገለገለው ፒርሎ ለብሔራዊ ቡድኑ 116 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡

በዚህም ለጣሊያን ብሔራዊ ቡድን በርካታ ጨዋታዎችን በማድረግ የሚበለጠው በስድስት ተጫዋቾች ብቻ ነው፡፡

በፈረንጆቹ 2006 የዓለም ዋንጫን ከጣሊያን ጋር ያሳካው ፒርሎ በፍጻሜው ጨዋታ የጨዋታው ኮከብ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ 15 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ከየትኛውም ጣሊያናዊ ተጫዋች ቀዳሚ ነው፡፡

አንድሪያ ፒርሎ የአሰልጣኝነት ስራውን በፈረንጆቹ 2020 የጁቬንቱስን ከ23 ዓመት በታች ቡድን በማሰልጠን መጀመሩ ይታወሳል፡፡

በመቀጠል የጁቬንቱስ ዋናውን ቡድን፣ የቱርኩን ፋቲህ ካራጉምሩክ እና ሳምፕዶሪያም ማሰልጠን ችሏል፡፡

አንድሪያ ፒርሎ በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ አንደኛ ዲቪዚዮን እየተሳተፈ የሚገኘውን ዱባይ ዩናይትድን እያሰለጠነ ይገኛል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version