አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን መመልከታችን ለሀገራችን ባለሀብቶች ለማስተዋወቅ ያግዘናል አሉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች፡፡
በኢትዮጵያ የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ የልማት እንቅስቃሴዎችን አምባሳደሮች እና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት እየጎበኙ ነው።
በጉብኝታቸውም በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ያለውን የኢንዱስትሪ ልማት፣ የፋብሪካዎች የሥራ እንቅስቃሴ እና በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶችን እየተመለከቱ መሆናቸው ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ዘመናዊ የኢንቨስትመንት ሥነ ምህዳር ለመፍጠር በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ላይ እያከናወነች ያለውን ሥራ ተመልክተዋል፡፡
ዞኖቹ ለኢንዱስትሪ እድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለውጭ ምንዛሪ ያላቸው አስተዋጽኦ በጉብኝቱ ወቅት ተነስቷል።
ቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን፣ የቂሊንጦ ልዩ ኢንዱስትሪያል ዞን፣ ኢስተርን ኢንዱስትሪያል ዞን፣ ጆይ ቴክ እና አይሲቲ ፓርክ መጎብኘታቸው ተመላክቷል፡፡
ጉብኝቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡
በክብረወሰን ኑሩ

