Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለመስጠት 667 የፈተና ማዕከላት ተዘጋጁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በ667 የፈተና ማዕከላት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው አለ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት÷ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን በ97 ዩኒቨርሲቲዎች እና በ570 የክልል ማዕከላት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚሰጠው ፈተና መደበኛ ተማሪዎችን ጨምሮ በሁሉም ፕሮግራሞች በተፈጥሮ ሳይንስ 306 ሺህ 964 እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስ 257 ሺህ 255 በድምሩ 564 ሺህ 219 ተማሪዎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

ፈተናውን በሙሉ አቅም በበይነ መረብ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ÷ በተለያዩ ምክንያቶች ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ በወረቀት የሚፈተኑ ተማሪዎች እንደሚኖሩም ጠቁመዋል።

በየክልሎች እና የፈተና ማዕከላት ያለው አቅም የተለያየ ቢሆንም በርካታ ኮምፒዩተሮች ለፈተና ዝግጁ እየተደረጉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ከባለፈው አርብ ጀምሮ ለተፈታኞች የበይነ መረብ የሙከራ ፈተና መሰጠት መጀመሩን አንስተዋል።

ፈተናው በ6 ዙር እንደሚሰጥና በማህበራዊ ሳይንስ በሶስት ዙር በተመሳሳይ በተፈጥሮ ሳይንስ ደግሞ በሶስት ዙር በመሆኑ አንድ ኮምፒዩተር ስድስት ተማሪን ያስተናግዳል ነው ሉት።

ተማሪዎች የፈተና ስርዓቱን እንዲለማመዱና ትምህርት ቤቶች እና ወላጆች ለተፈታኝ ተማሪዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version