አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ከተሞች የተጀመረውን የኮሪደር ልማት መርሐ ግብር ወደ ገጠር የሀገሪቱ ክፍሎች ለማስፋፋት እየተሰራ ነው።
የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ የገጠሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የተነደፈ ስትራቴጂያዊ የልማት እቅድ ሲሆን÷ በተለይም የገጠሩን ኢኮኖሚ ማነቃቃት፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦትን ማሻሻልና ከከተሞች ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር ላይ አተኩሯል።
በዚህም በጎንደር የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት የሕብረተሰቡን የአኗኗር ሂደት እየቀየረ ይገኛል።
በጎንደር ከተማ አስተዳደር የሳይና ሳቢያ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ደሴ ሲሳይ እና አቶ ዮሐንስ ባዜ በገጠር ኮሪደር ልማት ተጠቃሚ ከሆኑ አርሶ አደሮች መካከል ናቸው፡፡
አርሶ አደሮቹ የገጠር ኮሪደር ልማቱ በኑሯቸውና በአካባቢያቸው ላይ በጎ ተፅዕኖ መፍጠር መቻሉን አንስተው÷ በቀበሌያቸው የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ የመንገድ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የጤና ተቋማትና ሌሎች አገልግሎቶች የተሟሉበት መሆኑን ገልጸዋል።
የገጠር ኮሪደር ልማቱ የአኗኗር ዘይቤን የቀየረ መሆኑን ጠቁመው÷ የልማት ሥራዎችን በዘመናዊ መንገድ መከወን እንዲችሉ ዕድል መፍጠሩንም አስረድተዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ የተቋማት መሠረተ ልማትን ጨምሮ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ያሟላ መሆኑን አመላክተዋል።
በመጀመሪያው ዙር በተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ 5 ሞዴል አርሶ አደሮች ለስራና ለኑሮ ምቹ የሆኑ ቤቶች መረከባቸውን ገልጸው÷ የተገነቡ ቤቶችም ምቹ መኖሪያ ከመሆን ባለፈ ለሌሎች አካባቢዎች በተሞክሮ የሚወሰዱ ናቸው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመጋቢት ወር አጋማሽ በጎንደር ከተማ አስተዳደር ሳይና ሳቢያ የገጠር ቀበሌ የተገነቡ የገጠር ኮሪደር ሞዴል ቤቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸው ይታወሳል።
የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከተማዋን ብቻ ሳይሆን ገጠሩንም እኩል የማዘመን፣ የማስዋብና በልማት የማሸጋገር ሀገራዊ ራዕዕ በተግባር የታየበት መሆኑንም በወቅቱ ገልጸዋል።
የአካባቢውን ቁሳቁስ ከዘመናዊ መሃንዲስ ዕውቀት በማሰናሰል በአካባቢው በሚታወቀው የ”ደቢያት” የትብብር ባህል ደግሞ አርሶ አደሩን ቀጥታ በማሳተፍ እጅግ ዘመናዊ ቤቶች መገንባታቸውንም ተናግረዋል።

