Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከጥገኝነት ለመውጣት የታለመ ውሳኔ…

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዲጂታል ዘመን ዓለም በመረጃ ትዘወራለች፡፡ መረጃ ቀዳሚም ኋላ ቀርም ያደርጋል፡፡ አባት እናቶቻችን ዋጋ ከፍለው የሀገራችንን ሉዓላዊነት ጠብቀው አቆይተውልናል፡፡ አሁን በእኛ የዲጂታል ዘመን ደግሞ እኛ ነጻነታችንን ለማስጠበቅ እና ከጥገኝነት ለመውጣት መስራት ይኖርብናል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን የልማት ትልሞቿን እና ስኬቶቿን በመረጃና በአሃዛዊ ማስረጃ መሰነድ ጀምራለች፡፡ ይህ እርምጃ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በሌሎች በሚደገፉና በተበታተኑ የመረጃ ቋቶች ላይ የነበራትን ሙሉ ጥገኝነት የሚያስቀር እና ወደ ራሷ የዳታ ሉዓላዊነት የሚያሸጋግራት ስራ ነው፡፡

የዳታ ነጻነትን ማረጋገጥ ከጥገኝነት ራስን ወደ መቻል እና ለሌሎች ወደ መትረፍ ያሻግራል፡፡ ከመረጃና ከፖሊሲ ጥገኝነት፤ ከእጅ አዙር ተገዢነትም ያወጣል፡፡

በዚሁ መሠረት የሰው ወርቅ አያደምቅ ያለችው ኢትዮጵያ ዳታዋን መሰብሰብ፣ ማደራጀትና የመተንተን አቅም ላይ ደርሳለች፡፡ ይህንንም የምታደርገው ሉዓላዊነት በድንበርና በአካላዊ አቅም ብቻ እንደማይገነባ ስለምታምን ነው፡፡ የዳታ ሉዓላዊነት የምግብ እና የፖሊሲ ሉዓላዊነትንም ጭምር ያረጋግጣል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ቆጥራ ለማደራጀትና ለመተንተን እየሰራች ትገኛለች፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረጉ ምዘናዎች፣ ለድርድሮች፣ ለውጭ ኢንቨስትመንት ስበትና ለብድር አቅርቦት ጭምር ፋይዳውን የጎላ ያደርገዋል፡፡

ጅማሮው የኢትዮጵያን የመረጃ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ሀገሪቷ በራሷ መረጃ ላይ ተመስርታ እንድትወስንና የራሷን የልማት መስመር እንድትተልም አስችሏታል፡፡

ይህ ተግባር የዳታ ምስጢራዊነት እና የኢንክሪፕሽን አገልግሎቶች ደህንነት ተጠብቆ እንዲላኩ እና እንዲከማቹ፣ ከብሔራዊ ጥቅም አንጻር ታይተው እንዲተነተኑ፣ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እና የውሂብ አስተዳደራቸው ጤናማነት እንዲጠበቅ ዘመናዊ መፍትሄ ነው።

ይህ ስራ ራስን ወደ መቻል ለሚደረገው ጉዞ አንደኛው መንገድ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በተካሄደው የትናንቱ “የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት” ሀገራዊ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያስመገበቻቸውን ስኬቶችና የወደፊት አቅጣጫዎቿን ዳስሳለች።

Exit mobile version