አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አጋርነት የቀጣናውን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው አሉ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ሼኽ ሻኽቡጥ ቢን ናህያን፡፡
ሼኽ ሻኽቡጥ ቢን ናህያን ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ባለፉት ዓስር ዓመታት እያደገ መጥቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጋቢት ወር ላይ ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያደረጉት ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ግንኙነታቸውም በንግድ፣ በግብርና፣ በመሠረተ ልማት እና በኢነርጂ ዘርፎች ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመው÷ ቀጣይነት ያለውን እድገት እያሳየ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም የሁለቱ ሀገራት አመራሮች ግንኙነት ቀጣናውን ለማረጋጋት እና የጋራ ልማትን ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቅ መሆኑን ገልጸው÷ የሕዝቦችን ጥቅም የሚያስጠብቅ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በአፍሪካ ዘላቂ ልማት ላይ የረጅም ጊዜ ራዕይ በመያዝ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡
በቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባዔ ወቅት የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍና በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልማትን ለማስፋፋት የ1 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ መሰጠቱንም አስታውሰዋል፡፡
በአህመድ አቡዱልባር

