Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዲጂታል ኢንተለጀንስ መሠረተ ልማት ግንባታ በኢትዮጵያ…

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ግልጽ ፍኖተ ካርታ የያዘ ሉዓላዊ የዲጂታል ኢንተለጀንስ መሠረተ ልማት እየገነባች ነው አሉ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሜሮን ከፈለው (ዶ/ር)።

“የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት” በሚል መሪ ሐሳብ ኢትዮጵያ በመረጃና በስታቲስቲክስ የሉዓላዊነት ጉዞ ባስመዘገበችው ስኬት ላይ ያተኮረ ሀገራዊ ጉባኤ ተካሂዷል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ በዚህ ወቅት÷ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ መረጃን ለተጠቃሚ ሲያደርስ መቆየቱንና የተቋም ግንባታን አላማ በማድረግ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህም ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ተዓማኒ፣ እውነተኛ እና ወቅታዊ የመረጃ ምንጭ መሆናችንን እያረጋገጥን ጉዟችንን ወደፊት እንቀጥላለን ብለዋል።

ተቋሙ ከተበታተነና በወረቀት ከሚሠራበት አሠራር ወጥቶ በኮምፒውተር የታገዘ የግል ቃለመጠይቅ ሥርዓት፣ የጂኦግራፊያዊ መረጃ ሥርዓት ውህደት፣ የሪሞት ሰንሲንግ፣ የክላውድ መሠረ ተልማት መሸጋገሩን ተናግረዋል።

እንዲሁም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር በሀገር ውስጥ የቆጣሪዎች መከታተያ መድረክን በመጠቀም ወደ ሙሉ ዲጂታል እና ቅጽበታዊ የስታቲስቲክስ ሥነምህዳር ሽግግር ማድረጉን አብራርተዋል።

‎ኢትዮጵያ አሁን ላይ መረጃ በመሰብሰብ ላይ ብቻ እንዳልተወሰነችና ይልቁንም 26 በሀገር አቀፍ ደረጃ የተገናኙ ቅርንጫፎችን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚመራ የጥናትና ቆጠራ የመረጃ ቋት እያለማች መሆኑን አመልክተዋል።

ሀገሪቱ በዘመናዊ መሠረተ ልማት እምነት በሚጣልባቸው ስልቶች እና ብቃት ባለው የሰው ኃይል ላይ የተመሠረተ ግልጽ ፍኖተ ካርታ የያዘ ሉዓላዊ የዲጂታል ኢንተለጀንስ መሠረተ ልማት እየገነባች መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በሶስና አለማየሁ

Exit mobile version