አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራት እየገጠሟቸው ያሉትን የፋይናንስ ቀውሶች ቀድመው መከላከል እንዲችሉ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አሰራር መሻሻል አለበት አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ፡፡
ዓለም አቀፍ የአጋርነት ጉባኤ “21ኛውን ክፍለ ዘመን የሚመጥን ስርዓት መገንባት” በሚል መሪ ሀሳብ በለንደን እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ሀገራት እያጋጠሟቸው ያሉ ቀውሶችን ለመፍታት ችግሮችን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችልና ዘላቂ መፍትሄን የሚያመጣ የፋይናንስ ስርዓትን መፍጠር ይገባል፡፡
ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ፣ የጂኦፖለቲካዊ ክፍፍል፣ በእዳ ጫና እንዲሁም የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎልን በመሳሰሉ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ መሆኑን ጠቅሰው፥ እነዚህ ችግሮች በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን እንደሚጎዱ አስገንዝበዋል፡፡
ለተጽዕኖ የማይበገር አቅም መገንባት፣ ሉዓላዊነትና የጋራ ብልጽግና የማይነጣጠሉ ጉዳዮች ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ሀገራት በራሳቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የዜጎቻቸውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቂ ነፃነት ከሌላቸው ዕድገታቸውን ለማስቀጠል እንደሚቸገሩ አስረድተዋል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የተረጋጋ የዓለም ሁኔታ በነበረበት ወቅት መቋቋማቸውን አስታውሰው፥ አሁን ላይ ለሚከሰቱ ተደራራቢና ተለዋዋጭ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተቸገሩ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራትን በተናጠል ማከናወን ሀገራት ጠንካራና ራሳቸውን ችለው እንዳይቆሙ የሚያደርግ በመሆኑ፥ መሰል ተግባራት ከሀገራቱ ዕቅድና ተቋማት ጋር በወጥነት ሊተገበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራት የሀገራትን ሉዓላዊነት ያከበሩና ተጠያቂነትን ያረጋገጡ ሊሆኑ እንደሚገባ ታምናለች ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚን ማረጋጋት፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና የታዳሽ ኃይል ልማት ማስፋፋትን ጨምሮ እየተገበረችው የምትገኘውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተቀናጀ ዓለም አቀፍ አጋርነት መደገፍ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

