አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር በቤጅንግ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው ወቅት ፕሬዚዳንት ፑቲን ባደረጉት ንግግር÷ በሩሲያ እና ቻይና መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ አጋርነትና ስልታዊ መስተጋብር በዘመናዊው ዓለም የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ ምሳሌ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ በመከባበር እና በመተማመን ላይ የተመሰረተ እውነተኛ ትብብር ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ ዓላማውም የሀገራቱን ሕዝቦች ደኅንነት እና እድገት ማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ከውይይታቸው በኋላ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ የተለያዩ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን እየተፈራረሙ መሆናቸውን የሲጂቲኤን ዘገባ አመላክቷል፡፡
ቻይና እና ሩሲያ የምንጊዜም ወዳጅ ሀገራት ሲሆኑ÷ ሀገራቱ በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ወታደራዊ እና ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡
ቻይና የሩሲያን ነዳጅ በመግዛት ቀዳሚ የንግድ አጋር ስትሆን÷ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥም በዓመት ከ235 እስከ 240 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ የቢቢሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሚኪያስ አየለ

