1. የምርጫ ጣቢያውን ምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሰብሳቢነት ይመራል፤
2. የምርጫ አስፈፃሚዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን ይከታተላል፤ የሚፈፀሙ ስህተቶች ሲኖር የእርምት እርምጃ ይወስዳል፤
3. ጥፋት ወይም ቸልተኝነት በአስፈፃሚ ተፈፅሞ ሲገኝ ለምርጫ ክልል ኃላፊ ሪፖርት ያደርጋል፤
4. የተመደቡ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ሲጓደሉ በምርጫ ጣቢያው ወይም በምርጫ ክልሉ በተጠባባቂነት ከተያዙ የምርጫ አስፈጻሚዎች ጠይቆ እንዲተካለት ያደርጋል፤
5. መራጮች ድምፅ ከመስጠታቸው በፊት በምርጫ ጣቢያ ውስጥ ገለልተኛ በሆነ መልኩ ስለድምፅ አሰጣጥ ገለፃ ይሰጣል፤
6. የድምፅ መስጫ ሰነድና ቁሳቁስ ከምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት ወደ ምርጫ ጣቢያው በአግባቡ መድረሳቸውን ያረጋግጣል፤ የምርጫ ጣቢያው በድምፅ መስጫ ቀን ጥቅም ላይ የሚውሉ በቂ የድምፅ መስጫ ቁሳቁስና ሰነዶች እንዳሉት ያረጋግጣል፤
7. ከምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት የተረከባቸው ሁሉም ሰነዶችና ቁሳቁሶች ከድምፅ መስጫ ቀን በፊት ባለው ጊዜ ሁሉ ደህንነቱ በተረጋገጠ ስፍራ በአግባቡ ተጠብቀው መቀመጣቸውን ያረጋግጣል፤
8. በምርጫ ጣቢያው የድምፅ መስጠት ሂደቱን በሚገባ ለማከናወን የሚያስችል ምቹ የሆነ ስፍራ እንዳለው እንዲሁም በአግባቡ መሰናዳቱን ያረጋግጣል፤
9. በምርጫ ህጉ መሰረት በድምፅ መስጫ እለት በምርጫ ጣቢያው ውስጥ መገኘት ያለባቸው ሰዎች ብቻ መገኘታቸውን ያረጋግጣል፤
10 በድምፅ መስጫ ዕለት ጥቅም ላይ የሚውሉ የምርጫ ቁሳቁሶችና ሰነዶች በአግባቡ መያዛቸውን በመከታተል ስለአፈፃፀሙ ለምርጫ ክልሉ ሪፖርት ያደርጋል፤
11. የምርጫ ጣቢያው ደህንነትና ሥርዓት መጠበቁን ያረጋግጣል፤ ሰላምና ደህንነት እንዲያስከብሩ ለምርጫ ጣቢያው የተመደቡ የፖሊስ አባላት የእገዛ ጥያቄ በምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ካልቀረበላቸው በስተቀር ወደ ምርጫ ጣቢያው አለመግባታቸውን ያረጋግጣል፤
12. ወደ ምስጢር ድምፅ መስጫ ቦታ በአንድ ጊዜ ድምፅ የሚሰጥ መራጭ ብቻ መግባቱን ያረጋግጣል፤ ይቆጣጠራል፤
13. በድምፅ መስጫው ዕለት መጨረሻ ከድምፅ አሰጣጥና ቆጠራ ጋር የተያያዙ ሁሉም መረጃዎች በትክክል መመዝገባቸውን በማረጋገጥ ሰነዶችን እና የምርጫ ቁሳቁሶችን ለምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት ያስረክባል፤

