አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እንደ ምርጫ ባሉ ወሳኝ ሀገራዊ ሂደቶች የመገናኛ ብዙኃን ሚና እጅግ የላቀ ነው አሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን “ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት የመገናኛ ብዙኃን ሚና” በሚል ርዕስ በጋራ ያዘጋጁት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ለማስገንዘብ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ እንደ ምርጫ ባሉ ወሳኝ ሀገራዊ ሂደቶች የመገናኛ ብዙኃን ሚና እጅግ የላቀ ነው።
መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር፣ የዜጎችን የፖለቲካ ንቃት በማጎልበትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ስርዓት እንዲፈጠር በማድረግ በኩል ትልቅ አቅም አላቸው ነው ያሉት።
እንዲሁም በሀገር ግንባታ፣ ሕዝብን በማሳወቅና ለተግባር ለማነሳሳት የማይተካ ሚና እንዳላቸው ጠቁመው÷ በተለይም እንደ ምርጫ ባሉ ወሳኝ ሀገራዊ ሂደቶች የመገናኛ ብዙኃን ሚና እጅግ የላቀ እንደሆነ ገልጸዋል።
የምርጫ ሂደቱን ግልጽነት እና ተጠያቂነት ባለው መልኩ በመከታተልና በመዘገብ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በቀሪ የምርጫ ቀናትም ይህንኑ ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው÷ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕብረተሰቡን ዝግጁ በማድረግ በኩል በርካታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ይህ መድረክም የዛ አካል መሆኑን ጠቁመው÷ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

