አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ በአምቦ ከተማ አስተዳደር እና በምዕራብ ሸዋ ዞን የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የፓርቲው ደጋፊዎች ተገኝተዋል።
አቶ አወሉ አብዲ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ፓርቲው ባለፉት ዓመታት አካታች የፖለቲካ ሥርዓት በመገንባት፣ የሕግ የበላይነትን በማስፈንና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ስኬታማ ተግባራት አከናውኗል።
የሕዝብን የኑሮ ጫና ለመቀነስ የተካሄዱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በተለይም ዝቅተኛውን የሕብረተሰብ ክፍል በቀጥታ ተጠቃሚ ያደረጉ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳትን፣ የሰው ተኮር ፕሮጀክቶችንና የማኅበራዊ ደኅንነት ሥራዎችን በምሳሌነት አንስተዋል።
በተመሳሳይ ብልጽግና ፖርቲ ያዘጋጀው የምረጡኝ ቅስቀሳ በአፋር ክልል አይሳኢታ ከተማ ተካሂዷል።
በቅስቀሳ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ፓርቲው በተለይም ለአፋር አርብቶ አደሮች ያስገኟቸው ዘርፈ ብዙ ትርፋቶች የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከፓርቲው ጎን መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

