Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያ ክልል ከ11 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዷል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ በ2017/18 ምርት ዘመን የመኸር ወቅት በክልሉ 11 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት በተለያየ ዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ ነው አሉ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እንዳሉት፤ በአጠቃላይ በዘር ለመሸፈን ከታቀደው ውስጥ እስካሁን የ6 ሚሊየን ሄክታር መሬት ዝግጅት ተጠናቅቋል።
በክልሉ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው እርሻ ላይ አርሶ አደሮች በክላስተር ተደራጅተው በባለሙያ እገዛ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ለመካናይዜይሽን እርሻ ትኩረት በመስጠት በዘንድሮ ዓመት ብቻ በክልሉ 1 ሺህ 200 የእርሻ ትራክተሮች ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን ገልጸው፤ ይህም በክልሉ በእርሻ ስራ የተሰማሩ ትራክተሮችን ቁጥር 11 ሺህ በላይ አድርሶታል ብለዋል።
በተጨማሪም ለአርሶ አደሩ ዘንድሮ ለማቅረብ ከታቀደው 10 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 7 ሚሊየኑ ወደ ክልሉ መግባቱን አንስተዋል።
ከዚህ ውስጥ አሁን ላይ 3 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንደተሰራጨ አብራርተዋል።
በዛሬው ዕለት በጅማ ዞን ቦቶር ጦላይ ወረዳ ለመኸር እርሻ የተዘጋጀ መሬት በበቆሎ ዘር ለመሸፈን የማስጀመሪያ መርሐ ግብር የተካሄደ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት በዞኑ 883 ሺህ ሄክታር መሬት የመኸር እርሻ እየለማ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በወርቅአፈራው ያለው
Exit mobile version