አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በምርጫ ሂደት ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በውይይት እና በማስረጃ እየፈታሁ ነው አለ።
ዘንድሮ በሚካሄደው 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ እየተሳተፉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ምዝገባ ሂደት ላይ አጋጥመውናል ያሏቸውን ችግሮች እያቀረቡ ይገኛሉ።
በተለይም ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት (ትብብር) በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች በእጩዎች ምዝገባ ወቅት ዛቻና እንግልት ደርሶብኛል በሚል የቀረቡ አቤቱታዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
እነዚህን ቅሬታዎች በተመለከተ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት የብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ መለሰ ዓለሙ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በምርጫ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው ከተዋቀሩት የጋራ ምክር ቤቶች ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ በሚሆኑ ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች ላይ የጋራ ምክር ቤቶች መደራጀታቸውን ገልጸው፤ ፓርቲዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በማስረጃ ሲያቀርቡ በነፃነት ውይይት ተደርጎ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ ሳምንት ብቻ ለጋራ ምክር ቤቶቹ ከቀረቡት 69 የተለያዩ የፓርቲዎች አቤቱታዎችና ጉዳዮች መካከል 60ዎቹ ሙሉ በሙሉ መፍትሔ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ቀሪዎቹ 9 ጉዳዮች ደግሞ በሂደት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ እንዲሆን ገዢው ፓርቲ ትልቅ ኃላፊነት አለበት ነው ያሉት።
በምርጫው ሂደት ላይ እንቅፋት የሚፈጥሩ የብልጽግና ፓርቲ መዋቅር አካላት እና አባላት ሲገኙ ከማሰናበት ጀምሮ ተገቢው ጠንካራ አስተዳደራዊ ርምጃ እየተወሰደባቸው እንደሚገኝና ወደፊትም እንደሚቀጥል አቶ መለሰ ዓለሙ አረጋግጠዋል።
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየደረጃው ያሉትን የጋራ ምክር ቤት የችግር መፍቻ ሥርዓቶች ከመጠቀም ይልቅ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብቻ ጩኸት በመፍጠር ሂደቱን የማጠልሸት ሥራ ከመስራት በመቆጠብ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በሶስና አለማየሁ

