አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም የሕክምና ሙከራ ቀን በዛሬው ዕለት ተከብሮ ውሏል።
በየዓመቱ በፈረንጆች ግንቦት 20 የሚከበረው ቀኑ የሕክምና ምርምርና የሳይንስ ዓለም ለሰው ልጅ ጤና ያበረከቱትን አስደናቂ አስተዋፅኦ የምናስታውስበት ዕለት ነው።
ዕለቱም በፈረንጆች 1747 የመጀመሪያውን የተደራጀ የሕክምና ሙከራ ያካሄደውን ጄምስ ሊንድ ለማስታወስ የተመረጠ መሆኑ ይነገራል፡፡
ሊንድ በመርከበኞች ላይ የሚከሰተውን “ስከርቪ” የተባለ የቪታሚን እጥረት በሽታ ለማዳን ሎሚና ብርቱካን ጥቅም እንዳለው በሳይንሳዊ ሙከራ አረጋግጦ ነበር።
የሕክምና ሙከራ (Clinical Trial) አዲስ መድኃኒት፣ ክትባት ወይም የሕክምና ዘዴ ፈዋሽ መሆን ያለመሆኑ እንዲሁም ለሰው ልጅ ጤና መጠበቅ አስፈላጊ መሆን ያለመሆኑ የሚፈተንበት ሳይንሳዊ ሂደት ነው።
በዚህ ሂደት ሳይንቲስቶች እና ሐኪሞች “ይህ ሕክምና በእርግጥ ይሰራልን?” እና “ደኅንነቱ ተረጋግጧልን?” የሚሉ ጥያቄዎችን በጥንቃቄ ይመረምራሉ።
ዛሬ በሆስፒታሎች የምንጠቀማቸው በርካታ መድኃኒቶችና ክትባቶች በእነዚህ ሙከራዎች ውስጥ አልፈው ነው ወደ ሕዝብ የደረሱት።
ከካንሰር ሕክምና እስከ የወባ መድኃኒቶች፣ ከልብ በሽታ ሕክምና እስከ ኮቪድ-19 ክትባቶች ድረስ የሰው ሕይወትን ያዳኑ ግኝቶች ሁሉ ከሕክምና ሙከራ ጀርባ የተወለዱ የሙከራ ውጤቶች ናቸው።
በዚህ ሂደት ሕመምተኞች የሚወስዱት መድኃኒት ጉዳት እንዳያመጣ በጥንቃቄ ይፈተናል፤ ውጤታማ የሆነውንና ያልሆነውን በመለየት ለታካሚዎች የተሻለ አማራጭ ይቀርባል።
ዛሬ የሚደረጉ ሙከራዎች የነገውን ሕክምና ይወልዳሉ።
የካንሰር ኢምዩኖቴራፒ፣ ዘመናዊ ክትባቶች እና መሰል ህክምናዎች የዚህ ሂደት ውጤቶች ናቸው።
ብዙ ጊዜ ስለ ሕክምና ሙከራ ሲነሳ ትኩረቱ በሳይንቲስቶች ላይ ብቻ ይሁን እንጂ በሙከራዎች ውስጥ በፈቃደኝነት የሚሳተፉ ታካሚዎች እና ጤናማ በጎ ፈቃደኞች ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል፤ ያለ እነርሱ ዘመናዊ ሕክምና ሊኖር አይችልምና።
ዛሬ የምናከብረው የዓለም ሕክምና ሙከራ ቀን ሳይንስና እና ሰብዓዊነት ጥምረት ፈጥረው የሰው ሕይወትን እንዴት እንደሚያድኑ የሚታይበት ሲሆን÷ ዛሬ የምንጠቀማቸው መድኃኒቶች እና ሕክምናዎች ከብዙ ዓመታት ጥናትና ሙከራ በኋላ የተገኙ መሆናቸውንም ያስታውሰናል።
በኢትዮጵያ የሚካሄደው የህክምና ሙከራም የተሳካ እንዲሆን የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ባለስልጣን ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በመተባበር ቁጥጥርን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት ያከናውናል።
በዚህም በህክምና ሙከራ የሚሳተፉ ሰዎች ደኅንነት እና መብት ለመጠበቅ፣ የምርምሩን ሳይንሳዊ መሆንና ተዓማኒነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ደኅንነታቸው የተረጋገጠና ውጤታማ የሆኑ የህክምና ምርቶችን፣ ፈጠራና ግኝቶች ለጤና አገልግሎት እንዲውሉ እያስቻለ እንደሚገኝ የተቋሙ መረጃ ያመለክታል።
በአመለወርቅ ደምሰው

