አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አስቶን ቪላ ከ30 ዓመታት የዋንጫ ጥበቃ በኋላ ትናንት ምሽት የጀርመኑን ክለብ ፍሬቡርግ በማሸነፍ የዩሮፓ ሊግ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡
አሰልጣኝ ኡናይ ኢምሬ ላለፉት ዓመታት “የምንፈልገውን የሚያውቅ ምርጥ አሰልጣኝ አግኝተናል” በሚል በቪላ ደጋፊዎች ሲዘመርላቸው ቆይተዋል፡፡
ኡናይ ኢምሬ የአሰልጣኝነት ስራን የጀመሩት በተጫዋችነት ባሳለፉበት የስፔኑ ክለብ ሎርካ ዲፖርቲቫ ነበር፡፡
የሎርካ ዲፖርቲቫ ተጫዋች በነበሩበት ወቅት በጉዳት ምክንያት ከተጫዋችነት ራሳቸውን ሲያገልሉ ክለቡን እንዲመሩ በተሰጣቸው ኃላፊነት ነበር ወደ አሰልጣኝነት ሕይወት የገቡት፡፡
ከዚያ በኋላ አርሰናል እና ፒኤስጂን ጨምሮ በርካታ ክለቦችን በአሰልጣኝነት የመሩ ሲሆን፥ በተለይም በዩሮፓ ሊግ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ባሳኳቸው ድሎች የመድረኩ አለቃ ለመባል በቅተዋል፡፡
በተለይም የስፔኑን ክለብ ሴቪያ ከ2013/14 እስከ 2015/16 ለሦስት ተከታታይ የውድድር ዓመት የዩሮፓ ሊግ ሻምፒዮን ማድረግ ችለዋል፡፡
ኢምሬ አርሰናልን ጨምሮ ከተለያዩ ክለቦች ጋር በአጠቃላይ ስድስት ጊዜ ለዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ የደረሱ ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 2019 መድፈኞቹን እየመሩ በፍጻሜው በቼልሲ 4 ለ 1 ተሸንፈው ዋንጫውን ተነጥቀዋል፡፡
ከአርሰናል ስንብታቸው በኋላ ወደ ስፔን ተመልሰው የላሊጋውን ክለብ ቪያሪያል የተረከቡት ስፔናዊው አሰልጣኝ ከክለቡ ጋር ሻምፒዮን መሆን ችለዋል፡፡
ኢምሬ አስቶን ቪላን ከተረከቡ ወዲህ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ሻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ ክለቡ በቋሚነት በአውሮፓ መድረክ ተሳታፊ ለመሆን በቅቷል፡፡
አስቶን ቪላ ትናንት ምሽት በቱርክ ኢስታንቡል በተደረገው የዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ የጀርመኑን ክለብ ፍሬቡርግ በመርታት ከ30 ዓመታት በኋላ ዳግም ከዋንጫ ጋር ተገናኝቷል፡፡
ቪላዎች ከፈረንጆቹ 1996 ወዲህ ለ30 ዓመታት አንድም ዋንጫ ያላሳኩ ሲሆን፥ የምሽቱ ዋንጫ የአውሮፓ ዋንጫን (የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ) ካሸነፉ ከ44 ዓመታት በኋላ የተገኘ አህጉራዊ ዋንጫ ነው፡፡
የትናንት ምሽቱን ጨምሮ ስድስት ጊዜ በመድረኩ ለፍጻሜ የበቁት የ54 ዓመቱ አሰልጣኝ ለ5ኛ ጊዜ የዩሮፓ ሊግ ዋንጫቸውን አሳክተዋል፡፡
የጨዋታን ሚዛን መጠበቅ፣ ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ ሁሉንም የሜዳ ክፍል መቆጣጠር፣ በኃይል ተጭኖ ኳስን መንጠቅና በታክቲካዊ የቦታ አጠባበቅ ላይ የተመሰረተ የቡድን ጨዋታ ኡናይ ኢምሬ በስፋት የሚታወቁበት የእግር ኳስ ፍልስፍና መሆኑ ይነገራል።
አስደናቂ ጉዞ ላይ በሚገኘው ቡድናቸው ደስተኛ የሆኑት የቪላ ደጋፊዎች “የምንፈልገውን የሚያውቅ ምርጥ አሰልጣኝ አግኝተናል” በሚለው ሕብረ ዜማቸው የቪላ ፓርክ ተጨማሪ ድምቀት ሆነው ቀጥለዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

