አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር 5ኛውን የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ሰልጣኞች ምዝገባ መርሐ ግብር አስጀምሯል፡፡
በአስተዳደሩ የሳይበር ልሕቀት ማዕከል ዳይሬክተር ቢሻው በየነ በሰጡት መግለጫ÷ ስልጠናው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ለማሳካትና የኢትዮጵያን ዲጂታል ሉዓላዊነት ለማስከበር መሰረት የሚጥል ነው፡፡
የዘንድሮው ካምፕ የዲጂታል አካታችነት መርሕን በመከተል በክልል ደረጃ ከስድስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እንዲካሄድ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ሥልጠናው በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በባሕርዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሐረማያ እና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ለአንድ ወር እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
የሳይበር ደህንነት ቴክኖሎጂዎችን በመግዛት ብቻ የሚረጋገጥ አይደለም ያሉት ዳይሬክተሩ ÷ በሀገር በቀል እውቀት እና በሰለጠነ የሰው ኃይል የሚገነባ መሆኑን አስረድተዋል።
ለዚህም ፕሮግራሙ ኢትዮጵያ በዘርፉ በሰው ኃይል ራሷን እንድትችል ለማድረግና ነገ ሀገራቸውን ከጥቃት የሚከላከሉ ብቁ የሳይበር ሰራዊቶችን ለማፍራት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
ከወላጆችና ከት/ቤቶች እየቀረበ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎትና ተሳትፎ ከግምት ውስጥ በማስገባት የምዝገባ ሒደቱ ሰኞ ግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ጠቅሰዋል፡፡
እስካሁን ድረስ ከመላ ሀገሪቱ ከ4 ሺህ በላይ ታዳጊዎችና ወጣቶች መመዝገባቸውን ገልጸው ÷ የፕሮግራሙን ተደራሽነት ለማስፋት ዘንድሮ አዲስ አሰራር መዘርጋቱን አብራርተዋል፡፡
በሳይበር ደህንነት እና በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተለየ ተሰጥኦና ፍላጎት ያላቸው ታዳጊዎችና ወጣቶች የጊዜ ገደቡ ሳይጠናቀቅ እንዲመዘገቡም ጥሪ አቅርበዋል።
የመመዝገቢያ ድህረ ገጽ :- http://ctc.insa.gov.et/registration
በሔብሮን ዋልታው

