Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሀረሪ ክልል ቅርሶችን በማልማትና በመንከባከብ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት ተሰርቷል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀረሪ ክልል ቅርሶችን በማልማትና በመንከባከብ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል አለ የክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ።

በቢሮው የቅርስ ዳይሬክተር አሚር ረመዳን (ኢ/ር) እንዳሉት÷ በክልሉ ባለፉት ዓመታት ቅርሶችን በማልማትና በመንከባከብ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም በማሳደግ ረገድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

ከተከናወኑ ተግባራት መካከልም ዘመናትን ያስቆጠሩ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶችን ለጎብኚዎች ምቹና ማራኪ ለማድረግ የተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በክልሉ የሚገኙ ቅርሶችን በመንከባከብና በማልማት ረገድ የተከናወኑ ሥራዎችም ሐረርን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ያደረጉና የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ፍሰትና ገቢ እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ሕዝብን በማሳተፍ ከመንግሥት ምንም አይነት በጀት ሳይመደብለት ከ22 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ማልማት መቻሉንም ገልጸዋል።

6 ሺህ 114 ካሬ ሜትር የሚሸፍነውን የጀጎል ግንብ ዙሪያ መልሶ የማልማትና የአረንጓዴ ስፍራ እውን ማድረግ መቻሉን ገልጸው÷ በዚህም ከ7 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ጠቁመዋል።

የአካባቢ ሀብትና እውቀት በመጠቀም የተከናወኑም የቅርሱን ይዘትና ታሪካዊነት ውብ እንዲሆን ማድረግ መቻሉ አመልክተዋል።

በጀጎል መልሶ ማልማት የተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች ከተማዋ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ከማሳደግ ባለፈ ለነዋሪዎች የተመቸች እንድትሆን ያስቻለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

Exit mobile version