አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በ640 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው ዘመናዊ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ (ኢ/ር) እና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
ባለ 132/33 ኪሎ ቮልት የወራቤ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በከተማዋና አካባቢው ለዓመታት ይስተዋል የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና ጥራት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡
ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በከተማዋ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት መኖሩ አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስፋፋት ጉልህ ሚና አለው፡፡
ፕሮጀክቱ የወራቤ ከተማ አስተዳደር ባለፉት የለውጥ ዓመታት ካከናወናቸው ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሸብር ባልቻ (ኢ/ር) በበኩላቸው ÷ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ወደ ሥራ መግባቱ በወራቤ ከተማና ዙሪያ አስተማማኝና ጥራቱን የጠበቀ የኃይል አቅርቦት ለመዘርጋት ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
ጣቢያው ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን የቮልቴጅ መውረድና መቆራረጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚያቃልል መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በሊያ ዱጉማ

