አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰው ረቂቅ የሰላም ስምምነት በሆርሙዝ ሰርጥ መርከቦች በነጻነት እንዲተላለፉና በኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች በሂደት እንዲነሱ የሚያስችል ነው፡፡
እንዲሁም ስምምነቱ የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ ህጎችን ለማክበር ቁርጠኛ መሆንን ያካተተ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷ ሁለቱ ሀገራት ያልተግባቡባቸው ጉዳዮች ላይ በቀጣዮቹ ቀናት ድርድር እንደሚያደርጉ ተነግሯል፡፡
የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጣሂር አንዳራቢ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼባዝ ሸሪፍ በነገው ዕለት በቻይና በሚያደርጉት ጉብኝት በጉዳዩ ላይ እንደሚመክሩ አስታውቀዋል፡፡
ኢስላማባድ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ሰላም እንዲወርድ የምታደርገውን ጥረት ቤጂንግ እንደምትደግፍም ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ እና ኢራን ባሳለፍነው ወር አስቸኳይ የተኩስ አቁም ማድረግ፣ ድርድር እና ንግግርን ማደስ፣ በሆርሙዝ ሰርጥ የመርከቦች እንቅስቃሴ እንዲቀጥል፣ ንጹሃን እና ወታደራዊ ያልሆኑ ተቋማትን ከጥቃት መጠበቅ እንዲሁም ቀጣናውን ማረጋጋት በሚሉ ነጥቦች ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል፡፡
በሀገራቱ መካከል እየተካሄደ ያለው ድርድር መሻሻል እሳየ መሆኑ ቢገለጽም የኢራን የዩራኒየም ንጥረ ነገር ፕሮግራም እና አሜሪካ በሆርሙዝ ሰርጥ ቁጥጥር እንዲኖራት መፈለግ የድርድሩ ፈታኝ ጉዳዮች መሆናቸው መገለጹን የሻፋቅ ኒውስ ዘገባ አመላክቷል፡፡
በአቤል ነዋይ

