አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ፖሊሲዎችን ዘርግቶ ሀገርን ለማሻገር እየሠራ ነው አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
አቶ አረጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት መንግሥት በተደጋጋሚ ሁሉንም የሰላም አማራጮች እየተጠቀመ ነው፡፡
አሁንም ቢሆን ሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ ለሚመጣ አካል መንግሥት በሩ ክፍት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና እናቶች ወደ ጫካ የገቡትን ኃይሎች መምከር እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ዘመናዊ አሠራርን በመተግበር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ባሕር ዳር ከተማ ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ መሆኗን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ባለሃብቶች በስፋት ተሠማርተው ሊሠሩበት እንደሚገባ እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሕዝቡ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በከተማዋ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን እና ለወጣቶች እየፈጠሩት ያለውን የሥራ እድል አንስተው አመስግነዋል፡፡
በቀጣይም ከተማዋን የበለጠ በማስዋብ፣ ሰላምን በማረጋገጥ እና በሁሉም የልማት ሥራዎች ከመንግሥት ጎን ሆነው እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ድምጽ ከመስጠት ባሻገር ሰላምን ለማስጠበቅ በንቃት እንደሚሠሩ መናገራቸውንም አሚኮ ዘግቧል፡፡

