አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ‘የመደመር መንግሥት’ መጽሐፍ ወደ ዓረብኛ ቋንቋ መተርጎም የኢትዮጵያ እውነተኛ ገጽታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያስተዋውቃል አሉ።
አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሀገሪቱን ገጽታ በአሉታዊ መልኩ ለመሳል መሞከራቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም ‘የመደመር መንግሥት’ መጽሐፍ በዓረብኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለንባብ መብቃቱ ስለ ሀገሪቱ የሳሉትን አሉታዊ ገጽታ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ራዕይ ለመሻር ትልቅ መሣሪያ ነው ብለዋል።
የትርጉም ሥራው በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የዓረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገራትና ሕዝቦች የኢትዮጵያን የመደመር እሳቤ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ ጉዞ በጥልቀት እንዲረዱ ያስችላል ነው ያሉት።
በተለይም ከሀገራዊ ጥቅም አንጻር በዓረብ እና በቀጣናው ሀገራት ግልጽነትን ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና የባሕር በር ጉዳይን ጨምሮ የኢትዮጵያን አቋም ለማሳወቅ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች እና ከሌሎች የቀጣናው ሀገራት ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጥምረት እያጠናከረች መምጣቷን አንስተው፤ መጽሐፉ የኢትዮጵያን ራዕይ ለማስረጽ ምቹ መንገድ እንደሚፈጥር አምባሳደሩ አብራርተዋል።
መጽሐፉ ወደ ዓረብኛ መተርጎሙ 400 ሚሊየን የሚጠጉ የዓረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦችን እና ዓረብኛን የሥራ ቋንቋቸው ያደረጉ 25 ሀገራትን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል።
በኃይለየሱስ መኮንን

