አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመጠጥ ውሃ ተቋማትን የአገልግሎት ጊዜ ለማራዘም የሰለጠነ የሰው ሃይል ቁልፍ ሚና ይጫወታል አለ።
ባለፉት ዓመታት የውሃ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት በተከናወኑ ተግባራት ሀገራዊ የውሃ ተደራሽነት ሽፋን አድጓል።
እንደ ሀገር እስካሁን በክልሎች እና በፌደራል መንግሥት በጀት በተገነቡ የገጠር እና የከተማ የመጠጥ ውሃ ተቋማት 82 ሚሊየን 337 ሺህ 459 ህዝብ ተጠቃሚ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምሩ ፈቃዱ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ የውሃ ተቋማት የተለያየ እንከን ሲያጋጥማቸው በፍጥነት ተጠግነው ለአገልግሎት የሚያበቁ የቴክኒክ ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ ነው።
የውሃ መሰረተ ልማቶች ተገንብተው ወደ ስራ ከገቡ በኋላ ተገቢው ክትትል እና ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ በአግባቡ የሰለጠነ ባለሙያ ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢንስቲትዩቱ የዘርፉን ባለሙያዎች አቅም መገንባትን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በዓመት 2 ሺህ ያህል ባለሙያዎችን የማሰልጠን አቅም መፈጠሩን ገልጸው፤ በዚህም በሁሉም አካባቢዎች የተለያየ ደረጃ ያላቸውን ብልሽቶች መጠገን የሚችሉ ባለሙያዎች እየተፈጠሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከስልጠና ባሻገር ጥናትን መሰረት በማድረግ ለዘርፉ ተቋማት ድጋፍ መስጠት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ፣ የከርሰ ምድር ውሃ ፍለጋ እና የማሽነሪዎች ጥገና በኢንስቲትዩቱ እየተሰጠ እንደሆነ አብራርተዋል።
በኢንስቲትዩቱ የስልጠና እና ማማከር ዋና ስራ አስፈጻሚ አለማየሁ ጉደታ በበኩላቸው፤ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማጠናከር ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከተለያዩ አጋሮች ጋር በመተባበር ውጤታማ ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ለአብነትም በቅርቡ ወደ ተግባር የገባው ተቋማዊና አስተዳደራዊ አቅም ግንባታ ፕሮጀክት የኢንስቲትዩቱ አጋር በሆነው የጃፖን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቱ የውስጥ ገቢን በማመንጨት ራስን ለመቻል ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጥ ነው ብለዋል።
በአቢይ ጌታሁን

