Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በትኩረት እየሰራ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ በትኩረት እየሰራ ነው አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በግራንዴር ሴራሚክ ፋብሪካ ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢንቨስትመንት የኢኮኖሚው ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር ሆኖ የማህበረሰቡ አኗኗር እንዲለወጥ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት በተቀመጠው አቅጣጫ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ለኢንቨስትመንት የሚመጣው ባለሃብት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉንም ተናግረዋል።
ከለውጡ በፊት በክልሉ የነበረው የኢንቨስትመንት መጠን ከ10 ሺህ በታች እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ በተሰራው ስራ ከ43 ሺህ በላይ ኢንቨስትመንቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
የቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው የነቀምቴ ኢንዱትስሪ ፓርክ እንዲሁም የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለዚህ ማሳያ ናቸው ነው ያሉት፡፡
የክልሉ መንግሥት መሰረተ ልማቶች በማቅረብ እና ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እንዲሁም ወጣቱ ወደ ስራ እንዲሰማራ በማድረግ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዛሬ የተመረቀው ግራንዴር ሴራሚክ ፋብሪካም የዚሁ የትኩረት አቅጣጫ ውጤት ማሳያ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ክልሉን የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ በከፍተኛ ትጋት እየተሰራው ያለው ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አመልክተዋል።
በአቤል ነዋይ
Exit mobile version