አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በ3 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ የተቀናጀ የከተማ ግብርና ማዕከል ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ማዕከሉን መርቀው የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ማዕከሉ 16 ሱቆች እና 18 ሼዶችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተማችን ለሁሉም የምትመች የጋራ ቤታችን ናት፤ ልማታችንም አካታች ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ባለፈው ስርዓት ውስጥ አርሶ አደሩ የሚገፋበት መሬቱ ብቻ ተፈልጎ የሚዘነጋበት ሁኔታ እንደነበረ አስታውሰዋል።
ይህም ለለውጡ መምጣት ገፊ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩን በሁሉም የከተማ ልማት ውስጥ አካትተን አብሮ እንዲለማ እና ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ ከማድረግ ባሻገር ለልማት ሲነሳ ተገቢውን ካሳ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ በፊት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 14 ሺህ ሄክታር የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ልህቀት ማዕከልን መገንባቱን በአብነት አንስተዋል።
ይህ ዛሬ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ማዕከልም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
እነዚህን መሰል ማዕከላት በሌላ በኩል የከተማው ነዋሪ የሚያጋጥመውን የዋጋ ንረት ለመከላከል እና በተመጣጣኝ ዋጋ የግብርና ምርቶችን ለማቅረብ የሚያስችሉ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
ይህን መሰሉ አሰራር በጋራ ማደግን ተባብሮ መበልጸግን የሚያሳድግ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ይህንን ስራ ውጤታማ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

