Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

“በዐይኔ በብረቱ …!”

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም ማህበራዊ ጉዷንም፣ ገዷንም በድሯ ሸምና የሰው ልጅ የደረሰበትን ታላላቅ አብዮቶች ታስመለክተን ይዛለች ።

ይህ የዲጂታሉ ዘመን፣ አዲስ መስኮት ነው።

የዓለምን ታሪክ ሰፊ ንዋይ፣ ብዙ የሰው ኃይል እና ጊዜ በልቶ የመንገር ሩጫ በዚህ የመስኮት አቋራጭ በግለሰቦች ስልክና ካሜራ መዳፍ ላይ እየወደቀ ነው።

የማህበራዊ ትስስር ሜዳው ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬም ነገ ትተው ቢሄዱ ቆሞ አይጠብቅም። በዐይን ጥቅሻ ፈትለክ ነው። ለውጡ ፈጣን፣ ተለዋዋጭነቱ ነቅተው እንደ ቴኒስ ዳኛ ወዲህ ወዲያ አንገትዎን የሚነቀንቅ ሆኗል።

ወደ ምድረ ቀደምት ኢትዮጵያ የካሜራ ሌንሳቸውንና በሚሊየን የሚከተሏቸውን ዐይን ይዘው የሚመጡ የመስኮቱ ዘዋሪዎች ለኢትዮጵያ አዲስ ነጋሪት የሚጎስሙ ናቸው።

በሚሊየን የሚቆጠሩ ተከታዮቻቸው በየሰከንዱ ለሚለቀቁ ይዘቶች ሲሉ ዐይንና ጆሯቸውን በእነዚህ የዘዋሪዎች ዳና ላይ አድርገዋል።

ምክንያቱም ዓለም የዲጂታል ዝመና አብዮቷ ላይ ወደ ፊት እንጂ የኋልዮች ዳራዋን ለመመልከት አፍታም የላትም፤ ተከታዮቻቸውም ጊዜ የለቸውም። አጭር፣ ፈጣን፣ አዲስ ይናፍቃሉ።

የአሜሪካው ታዋቂ የቀጥታ ስርጭት አቅራቢ አይሾው ስፒድ፣ እንዲሁም ከ19 ሚሊየን በላይ የቲክቶክ ተከታዮች ያሉት የዲጂታል ዜና አቅራቢው ዲላን ፔጅ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዲጂታል ዲፕሎማሲና የቱሪዝም ስበት ማዕከል እየሆነች መምጣቷን የሚያሳይ ትልቅ የጂኦፖለቲካዊና የማኅበራዊ ሚዲያ ለውጥ ማሳያ ተደርጎ የሚቆጠር ነው።

ቀድሞ በኢትዮጵያ ፍቅር የወደቀው ብሪታኒያዊው የቲክቶክ ዜና አቅራቢ ዲላን ፔጅ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና ስለ ኢትዮጵያውያን የአንድነት መንፈስ በአዎንታ በመዘገብ መንፈሱ ከአካሉ ቀድሞ አዲስ አበባ ከደረሰ ከርሟል።

ይህ ፕሮጀክት በውጭ ዕዳ ሳይሆን በሕዝብ ቦንድና በላብ የተገነባ ነው በማለት አጉልቶ አሳይቷል።

ግድቡንም “በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የሚቀይረው የአፍሪካ የብርሃን ተስፋ” በማለት ለዓለም ማስተዋወቁን አንረሳም።

ዲላን በርካታ ቀናትን የሚወስደውን ታላቁን ጉዞዬን፣ በቅኝ ግዛት ባልተገዛችው ሀገር ኢትዮጵያ ጀምሬያለሁ በማለት ወደ አዲስ አበባ ሲገባ ይዞት የመጣው የካሜራ ሌንስ የኢትዮጵያን ጥንታዊነት ብቻ ሳይሆን አዲሱን የቴክኖሎጂ ምዕራፍም ጭምር የገለጠ ሆኗል።

በአዲስ አበባ ቆይታው የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በጎበኘበት ወቅት፥ ይህን በቴክኖሎጂ የተቃኘ ቦታ ሳየው ተደምሜያለሁ፤ አፍሪካ ተቀይራለች፣ አዲሱን ገፅታዋን ለዓለም የሚያሳይ ቦታ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል።

አዲስ አበባ በቅርቡ ከ30 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡና በጥምረት ከ470 ሚሊየን በላይ ተከታዮች ያሏቸው ከ200 በላይ የዲጂታል ፈጣሪዎች የተሳተፉበትን የአፍሪካ ማኅበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪዎች ጉባኤን ማስተናገዷ የይዘት ፈጣሪዎች የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ አድርጓታል።

በጉባኤው ላይ በቀረቡ መረጃዎች መሠረት ስለ አፍሪካ የሚሰራጩ የተዛቡና አሉታዊ ትረካዎች በአህጉሪቱ ላይ በየዓመቱ እስከ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ የኢኮኖሚ ኪሳራ ያደርሳሉ።

ዲላን ፔጅ እና መሰል የይዘት ፈጣሪዎች ይህንን የተዛባ ምስል ለመስበር ‘ሳይነገራችሁ በዓይናችሁ እዩት’ በሚል መርህ እየመጡ ነው።

የዲላን ፔጅ ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን እንደ አዶናይ ያሉ የሀገር ውስጥ ይዘት ፈጣሪዎች የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው።

የተጽእኖ ፈጣሪዎች ጉብኝት የዲጂታል ዲፕሎማሲና የሀገር ገፅታ ግንባታ ወሳኝ ተግባር ሲሆን፥ የወቅቱ የሀያላን ሀገራት ፉክክር ገር ኃይል መሆኑን ላጤነ ዲፕሎማሲው ይገለጥለታል።

ገር ዲፕሎማሲ ሰዎችን ሳያስገድዱ፣ ወደውና ፈቅደው አንተ የምትፈልገውን ነገር እንዲያደርጉ የማድረግ ብቃት መሆኑን የጽንሰ ሀሳቡ ፈጣሪ አሜሪካዊው ጆሴፍ ናይ ያስረዳሉ።

ለጆሴፍ ምስጋና ይግባውና ሀገራት ከጦር መሳሪያ እሽቅድምድሞሽ ወደ ለስላሳው አቀራረብ ፊታቸውን እንዲያዞሩ አድርጓል።

ከአሜሪካ ገር መንገዶች መካከል ሆሊውድ፣ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ብራንዶች (አፕል, ጎግል, ማይክሮሶፍት)፣ ምግቦች (ማክዶናልድ፣ ኮካ ኮላ) እና ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ይጠቀሳሉ።

ለደቡብ ኮሪያ “ሃሊዩ” ወይም የኮሪያ ማዕበል። ይህም የኬ-ፖፕ ሙዚቃ፣ የኮሪያ ፊልሞችና ድራማዎች እንዲሁም የውበት ምርቶች፤ ለብሪታንያ የእንግሊዝኛ ቋንቋ፣ ቢቢሲ እና የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ገሩ መንገዳቸው ነው።

ሳዑዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እንደ ማንችስተር ሲቲ እና ኒውካስል ዩናይትድ የእግር ኳስ ክለቦችን በመግዛት እንዲሁም የዓለም ዋንጫዎችን በማዘጋጀትና እንደ ሮናልዶ ታዋቂ ተጫዋቾችን ወደ ሀገራቸው በማምጣት የዓለምን ትኩረት በመሳብ የሀገራቸውን ገጽታ እያደሱ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያም ምድረ ቀደምት፣ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት የአድዋ ድል፣ የፓን-አፍሪካኒዝም ማዕከል መሆኗ፣ የቡና መገኛነቷ፣ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎቿን በማስተዋወቅ የራሷን የዲጂታል ለስላሳ ኃይል እየገነባች ትገኛለች።

በዚህም በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ መነቃቃትን ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ ይህንን ወርቃማ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ዕድል በመጠቀም፣ የቱሪዝምና የኢኮኖሚ ምሰሶዎቿን ለማጠናከር በጥበብና በስልታዊ መሪነት ልትራመድበት ይጠበቃል።

ዲጂታሉ ዓለም በሮችን ከፍቷል፤ የኢትዮጵያን መልኮች በአዲሱ ነጋሪት ማስተጋባት የዛሬ ስራ ነው ።

በኃይለኢየሱስ መኮንን

Exit mobile version