Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሁላችንም ከመለያየት ይልቅ አብሮነት ላይ ማተኮር ይኖርብናል – ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁላችንም ከጥላቻ ንግግር ይልቅ የሐሳብ የበላይነት፤ ከመለያየት ይልቅ አብሮነት ላይ ማተኮር ይኖርብናል አሉ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ “ሃይማኖታዊ ዕሴቶቻችን ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ ሐሳብ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የአደባባይ የሰላምና አብሮነት የጸሎት መርሐ ግብር በአዲስ አበባ አራዳ ፓርክ እየተካሄደ ነው።

ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ ዛሬ ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ይዞት በመጣው ፈተናና ዕድል ፊት ለፊት እንገኛለን።

የኢትዮጵያዊያን የጋራ አጀንዳ ዘላቂ ሰላምና ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ሃይማኖታዊ እሴቶችን ማጽናት መሆን ይገባል ነው ያሉት።

ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ባደረጉት ንግግር 98 በመቶ አማኝ ሕዝብ ያለበት ሀገር እንደመሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ለሀገር ሰላም በአብሮነት መቆም አስፈላጊ በመሆኑ በአንድነት ለሀገር ሰላም ልንጸልይ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊነት የማይደፈር የክብር ተራራ፣ የነጻነት ዓርማና የማይደበዝዝ የታሪክ ዐሻራ ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው÷ ይህ አንድነት በመከራ ጊዜ ይበልጥ የሚጸና በደስታ ጊዜ እንደተዋበ እንቁ የሚደምቅ በጦርነት አውድማ ላይ ደግሞ ከብረት መከታነት የላቀ ጥንካሬ ያለው መሆኑን አመልክተዋል።

በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በባሕል ብንለያይም በኢትጵያዊነት ጥላ ስር እሱ፤ እሷ ኢትዮጵያዊ ናት ተብለን ከሩቅ የምንለይበት ልዩነታችን በእርቅ የሚፈታ፣ ኩርፊያችን እንደማለዳ ጤዛ የሚያስረሳ ህያው ፍቅር የተገነባ የማይጠፋ እሴቶች ባለቤቶች ነን ሲሉም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ለእኛ የማትቆረስ የስስት እንጀራ ናት ያሉት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ÷ ኢትዮጵያዊነት ለነገ ቸል የማንለው የልብ ምታችን እንደሆነ ወዳጅም ጠላትም ያውቀዋል ብለዋል።

ድህነትን በመዋጋት የሀገርን ዕድገት ለማረጋገጥ በጸሎትና በስራ ትጋት መበርታት እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሁላችንም ከጥላቻ ንግግር ይልቅ የሐሳብ የበላይነት፣ ከመለያየት ይልቅ አብሮነት ላይ ማተኮር ይኖርብናል ሲሉም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ልማትና ፍትህ ማረጋገጥ እንጂ የትናንትናን ስብራት እያስታወሰ ተስፋ የሚያስቆርጠውንና ቁስሉን የሚያክበትን ገል የሚያቀርብለትን አይደለም ሲሉም ገልጸዋል።

በመርሐ ግብሩ የጉባኤው አባል ቤተ ዕምነቶች የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ እንዲሁም የፌደራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች ተገኝተዋል።

በአድማሱ አራጋው

Exit mobile version