አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አጀንዳ ሲያሰባስብ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡
ኮሚሽኑ በዚህ ሂደት በሀገራችን ኢትዮጵያ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ባልተግባቡባቸው እጅግ መሠረታዊ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የምክክር አጀንዳዎቻቸውን እንዲሰጡ መደላድል ፈጥሯል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ኮሚሽኑ የተሰበሰበውን አጀንዳ አጠናክሮ እና ቀርፆ በማጠናቀቅ በምክክር ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ያሻል ያላቸውን አዘጋጅቷል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ይመጥናሉ ብሎ የቀረፀውን ረቂቅ አጀንዳ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማቅረብ ግብዓት በማሰባሰብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ሂደት ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ብሎም ለአጀንዳ ቀረፃ የተለያዩ አበርክቶዎች እንደሚኖሩት የሚታመን ሲሆን የሚከተሉት ሃሳቦች ይህንን ያብራራሉ፡፡
👉የአጀንዳ ሃሳቦች ትክክልኝነትን ከማረጋገጥ አንፃር
የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በርካታ ጉዳዮች በአጀንዳነት እንዲያዝላቸው ማቅረባቸውን ተከትሎ ያቀረቧቸው ሃሳቦች በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለማወቅ ጉጉት ማሳደራቸው አጠያያቂ አይሆንም፡፡
በመሆኑም መሰል ተግባራት እና መድረኮች ኮሚሽኑ የባለድርሻ አካላትን አጀንዳ በአደራ ተረክቦ ሲቀርፅ በተፈለገው ቅርፅ ለታለመው ዓላማ መዘጋጀታቸውን ከእነዚሁ ባለድርሻ አካላት ጋር ማረጋገጡ ለምክክሩ ሂደት ጉልህ ሚናን ይጫወታል፡፡
👉የሂደቱን ባለቤትነት ከማዳበር አንፃር
የሀገራዊ ምክክር ረቂቅ አጀንዳን ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት አቅርቦ ማስተቸት እና በሂደቱ የእነዚህን አካላት ይሁንታ ለማግኘት መሻት ባለድርሻ አካላት በሂደቱ ላይ ያላቸውን የባለቤትነት መንፈስ ያጠናክርላቸዋል፡፡ ይህም ሁሉም አካላት በሂደቱ የሚኖራቸውን ሚና እንዲያጎለብቱ ያስችላቸዋል፡፡
👉ግልፅነትን ከማጠናከር አንፃር
ባለድርሻ አካላት በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የሚመካከሩባቸውን የአጀንዳ ሃሳቦች ቀድመው ማወቃቸው እና ስለትክክለኛነታቸውም ይሁንታን መስጠታቸው ሂደቱን ግልፅ እና ተዓማኒ እንዲሆን ያግዘዋል፡፡

