Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለዓረፋ በዓል የምርት እጥረት እንዳያጋጥም እና የተረጋጋ ግብይት እንዲኖር ዝግጅት አድርገናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል የምርት እጥረት እንዳያጋጥም እንዲሁም የተረጋጋ ግብይት እንዲኖር ዝግጅት አድርገናል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ የከተማ አስተዳደሩ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ለ1 ሺህ 447ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል ምክንያት በማድረግ ነዋሪዎቻችን በዓሉን ያለምንም የገበያ ጫና እና እንግልት በደስታ ማክበር እንዲችሉ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች እና የበዓል ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እና በበቂ መጠን እንዲቀርቡ ሰፊ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።

በተለይም በከተማዋ በሚገኙ 7ቱም የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት የሰብል፣ የጥራጥሬ፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርቶች በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረቡን ገልጸዋል።

ሸማቾች በቀላሉ በአቅራቢያቸው መገብየት እንዲችሉ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ 250 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ ክፍት ሆነው እንዲሰሩ መደረጋቸውንም አመልክተዋል።

በ2 ሺህ 52 የሸማቾች ሕብረት ስራ ማህበራት ሱቆች እና በአዲስ አበባ ንግድ ስራዎች ድርጅት መጋዘኖች አማካኝነት የዘይት እና የዱቄት ምርቶች በበቂ መጠን ተደራሽ ሆነዋልም ነው ያሉት።

በመሆኑም የከተማዋ ነዋሪዎች ከተጠቀሱት የገበያ አማራጮች በአቅራቢያቸው ከሚገኙት መጠቀም እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

Exit mobile version