አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት ዙር ከተሰራ የኮሪደር ልማት ሥራ ጋር ተያይዞ ደረጃቸውን የጠበቁ የትራንስፖርት ተርሚናሎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
የከተማ አስተዳደሩ መንገዶች ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እያሱ ሰሎሞን ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ ተርሚናሎቹ ቀደም ሲል የነበረውን የመንገድ መጨናነቅ እና አደጋ ይቀንሳሉ።
በመዲናዋ በአጠቃላይ ከ6 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ 45 ተርሚናሎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አንስተዋል።
ተርሚናሎቹ በቂ የሆነ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን ጨምሮ የተሳፋሪዎች ማረፊያ፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ ካፌዎች እና የትኬት መቁረጫ ቢሮዎች ማካተታቸውን ጠቅሰዋል።
ከታክሲ መነሻ ተርሚናሎች በተጨማሪ በየፌርማታው ከዋናው መንገድ ገባ ብለው የተሠሩ 152 መጫኛና ማውረጃ ቦታዎች የትራንስፖት ሥርዓቱ እንዲሳለጥ ማስቻላቸውን ገልጸዋል።
ተርሚናሎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ፣ ለአካባቢው ውበት የሚጨምሩ፣ ምቹ፣ ዘመናዊ እና የትራፊክ መጨናነቅን የሚቀንሱ እንደሆኑም አመልክተዋል።
ቀደም ሲል ተሳፋሪዎችን በዋና መንገዶች ዳር ያወርዱ እና ይጭኑ የነበሩ ታክሲና አውቶቡሶች አሁን ላይ በተደራጀና ለተገልጋዮችም ሆነ ለአገልግሎት አቅራቢዎች ምቹ በሆነ ስፍራ መጠቀማቸው ለመዲናዋ ተጨማሪ ውበት ሆኗልም ነው ያሉት።
የተገነቡ መሰረተ ልማቶች የተጠቃሚው ሕዝብ እንደመሆናቸው በአግባቡ መጠቀምና መንከባከብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በበጸሎት መንገሻ
አቶ እያሱ ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ሙሉ ቆይታ ከታች ባለው ሊንክ ይከታተሉ👇
https://www.youtube.com/watch?v=CvkNY76kAI0

