አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ማህበረሰቡ ያለምንም ስጋት መምረጥ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል አለ የክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ፡፡
የክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ÷ በምርጫ ወቅት የክልሉ ፖሊስ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በክልሉ ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ እስከ ምርጫ ቅስቀሳ የማጠቃለያ ዕለት የታየው የማኅበረሰቡ የነቃ ተሳትፎና ፍጹም ሰላማዊ ድባብ በምርጫው እለትና ከምርጫው በኋላም ቀጣይነት እንዲኖረው ፖሊስ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት፡፡
የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዳራሽም እና በጎዳና ያደረጓቸው የምረጡኝ ቅስቀሳ መርሀ ግብሮች በስኬት እንዲጠናቀቁ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ እስከ ምርጫ ቅስቀሳ የድጋፍ ሰልፎች ያሳየው የነቃ ተሳትፎ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እንዲመሠረት ያለውን ጽኑ እምነት የሚያሳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ምርጫን ብቸኛ አማራጭ በማድረግ የሄደበት ርቀት የሰላም አማራጭን ለማይደግፉ ኃይሎችም ትልቅ መልስ ነው ብለዋል።
ማኅበረሰቡ በቅድመ ምርጫ ያሳየውን የነቃ ተሳትፎ በማስቀጠል በምርጫው ዕለት በነቂስ ወጥቶ መምረጥ እንዲችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አረጋግጠዋል፡፡
የምርጫውን ሰላማዊ ሁኔታ ለማወክ የሚሠሩ ኃይሎችን ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ዓላማቸው እንዳይሳካ ሕዝቡ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
መራጩ ሕዝብ በሀሰተኛ መረጃ ሳይታለል የሚጠበቅበትን እንዲወጣ አመልክተው፤ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በደሳለኝ ቢራራ

