አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የነገሌ ቦረና ገዳ የአውሮፕላን ማረፊያው መንግሥት ለአርብቶ አደሩ የሰጠውን ትኩረት በተግባር ያረጋገጠ ነው አሉ የምስራቅ ቦረና ዞን ነዋሪዎች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አየር መንገድ 24ኛ የሀገር ውስጥ መዳረሻ የሆነውንና አዲሱን የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያውን በዛሬው ዕለት በይፋ መርቀዋል።
የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪው እንዳለ መገርሳ የአውሮፕላን ማረፊያው በየብስ ትራንስፖርት ረጅም ጉዞ ምክንያት ይደርስ የነበረውን እንግልትና ችግር በእጅጉ የሚያቃልል እንደሆነ ተናግረዋል።
ዞኑ በእንስሳት ሀብትና የስንዴ ምርት የሚታወቅ ቢሆንም ምርቱን ለማጓጓዝ የትራንስፖርት እጥረት ያጋጥም እንደነበር አስታውሰው÷ አውሮፕላን ማረፊያው የምርት ዝውውርን የበለጠ እንደሚያቀላጥፍ አንስተዋል።
ይህም ለአካባቢው ኢኮኖሚና ቱሪዝም እድገት ካለው አስተዋጽኦ ባሻገር የመንገደኞችን ጉዞ ምቹ፣ ቀላልና ፈጣን እንደሚያደርገው እና በዚህም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ሌላኛው የነገሌ ቦረና ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ፈንታ ገረመው በበኩላቸው÷ የአውሮፕላን ማረፊያው ስራ መጀመር የዞኑን ልማትና እድገት እንደሚያፋጥንና በተለይም የነገሌ ቦረና ከተማን የንግድና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
በዞኑ ሊበን ወረዳ ነዋሪ ቢሉ ቢርቢርሳ የአውሮፕላን ማረፊያው መንግሥት ለአርብቶ አደሩ አካባቢ የሰጠውን ትኩረትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ የምርቶችና ግብአቶች እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ በማድረግ ተጨማሪ አቅም የሚሆን ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

