አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ ይገኛል፡፡
የክልሉ ምርጫ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ አቶ አብርሃም አንጁሎ እንደገለጹት÷ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመጭው ሰኞ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
በክልሉ የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው÷ የቁሳቁስ ስርጭቱ በጥንቃቄና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በጸጥታ ኃይል ታጅቦ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተጓጓዘ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የድምጽ መስጫ ወረቀትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመሰራጨት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ጽሕፈት ቤቱ በተደራጀ መልኩ የቅደመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ በሚገኙ 56 የምርጫ ክልሎች 3 ሺህ 941 የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን አንስተው÷ በበሁሉም ምርጫ ጣቢያዎቹ የፊታችን ሰኞ ድምጽ እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
ዜጎችም በምርጫው ዕለት የነቃ ተሰትፎ በማድረግ በወሰዱት ካርድ ድምጽ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በማስተዋል አሰፋ

