አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ውጤታማነት የመንግሥት፣ የግል እና ሃይማኖታዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል አሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)።
ኮሚሽኑ በዋናው ሀገራዊ ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ ረቂቅ አጀንዳዎችን በተመለከተ ከተባባሪ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት÷ የኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በስኬት መከናወኑን ገልጸው÷ ለምክክር ሂደቱ ውጤታማነት የመንግሥት፣ የግልና የሃይማኖት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራን ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በተቋማት እና ማህበራት፣ በወረዳ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በዲያስፖራ ማህበረሰብ፣ በመንግሥት ተቋማት እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰበሰብ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
ሂደቱ ከነበረው ዕቅድ አንጻር በስኬት ተከናውኗል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ÷ ይህም በቀጣይ ለሚካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ መሰረት የተጣለበት መሆኑን አመልክተዋል።
ኮሚሽኑ በተለያዩ ሕብረተሰብ ክፍሎች ሲያከናውናቸው የቆዩትን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶች በማጠናቀቅ አሁን ላይ የተለዩትን ዋና ዋና የሀገራዊ ጉባኤ አጀንዳዎች ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት እያቀረበ እና ተጨማሪ ግብዓቶችን የመሰብሰብ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ባለው አዲስ ምዕራፍ ኮሚሽኑ ያዘጋጃቸውንና ያደራጃቸውን የአጀንዳ ረቂቆች ለተባባሪ ባለድርሻ አካላት እያቀረበ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ይህንን የግብዓት ማሰባሰብ ሂደት ካጠናቀቀ በኋላ የተገኙትን አዳዲስ ሐሳቦች በማካተት ለመጨረሻውንና ዋናውን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አጀንዳ እንደሚያቀርብ አመላክተዋል፡፡
በዚህም በተደራጀው አጀንዳ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ተወካዮች በሚሳተፉ ሲሆን÷ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ቀርቦ ምክክር እንደሚደረግበትም ጠቁመዋል።
በሳራ ስዩም

