አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምታደርገው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለአህጉሪቱምወሳኝ ነው አሉ የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢዎች መሪ ኡሁሩ ኬንያታ።
መጪው ሰኞ የሚካሄደውን 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ የተሰየመውን የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድንን በሊቀመንበርነት የሚመሩት የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ትናንት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።
ኡሁሩ ኬንያታ በዚህ ወቅት በሰጡት አስተያየት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ ለአህጉሪቱ የተለያዩ ተቋማት መቀመጫ የሆነች ቤታችን ናት።
ኢትዮጵያ የምታደርገው 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለአህጉሪቱም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው÷ እህት እና ወንድሞቼ መካከል በመገኘት ምርጫውን ለመታዘብ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የሚበጃቸውን መምረጥ የሚያስችል ጥበብ ያላቸው ሕዝቦች መሆናቸውን ገልጸው÷ ኢትዮጵያ በምታደርጋቸው የለውጥ ስራዎች ለቀሪ አፍሪካውያን ምሳሌ መሆን የምትችል ሀገር ናት ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
አፍሪካ ሕብረት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አህጉሪቱ የሚከናወኑ የምርጫ ሂደቶችን በመሳተፍ እና በመታዘብ የሚቀጥል መሆኑን በማንሳት ዓላማውም የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማስረጽ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በእያንዳንዱ ሀገር ያለን መልካም ተሞክሮ ለመለዋወጥና ለመማማር እንደሚረዳ ጠቁመው÷ ይህም ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የመስጠት አንድ አካል መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የአፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታ ከሌላው ዓለም ጋር የሚለያይ በመሆኑ የሌላውን ዓለም ተሞክሮ መገልበጥ አይጠበቅብንም ያሉት ኡሁሩ ኬንያታ÷ ይልቁንም የእኛን አህጉር መልካም እሴቶች መለዋወጥና መማማር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚደረገው ምርጫ ሕዝቡ ሐሳቡን በነጻነት የሚገልጽበትና ሀገሪቱም የዴሞክራሲ ግንባታዋን መሰረት የምትጥልበት እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
በአቤል ነዋይ

