አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምርጫና ድህረ ምርጫ ቀናት በሚከናወኑ የፀጥታ ማስከበር ተግባራት ምርጫው በስኬት እንዲከወን አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል አለ የአዲስ አበባ ፖሊስ፡፡
በአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በቅድመ ምርጫ የተከናወኑ ተግባራትን ለመገምገም በተዘጋጀው መድረክ ላይ እንደተገለጸው÷ የምርጫና ድህረ ምርጫ ቀናት የጸጥታ ማስከበር ተግባራት በስኬት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡
የጸጥታ አካላት አስቀድመው የጋራ ዕቅድ በማውጣት ወደ ተግባር በመግባታቸው ቅድመ ምርጫውን በጥሩ ሁኔታ ማከናወን እንደተቻለ ተመላክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌ/ጄነራል አስራት ደኔሮ÷ የምርጫን ደህንነት የማረጋገጥ ተግባር ልዩ ጥንቃቄን የሚሻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቀሪ ተግባራት ካሉ በአስቸኳይ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበው÷ በምርጫው ላይ አሉታዊ ጫና ለማሳደር የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እንዳሉ በመረዳት በምርጫ ዕለት እና ድህረ ምርጫም ሂደቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የከተማው ሠላምና ጸጥታ ቢሮ አስተዳደር ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው÷ የጸጥታ ሥራው ለሕብረተሰቡ ደህንነትን ያረጋገጠ እና ለፀረ ሠላም ኃይሎች ጫናን የሚያሳድር መሆን እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
በተለይ ፀጉረ ልውጦችን ለመቆጣጠር በሸገር ከተማ ሥር ከሚገኙ ክፍለ ከተሞች ጋር ያለውን ትስስር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡
ምርጫው ያለ ምንም የፀጥታ እንከን እንዲከናወን ሕብረተሰቡ ማንኛውም ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በነጻ የስልክ መስመሮች 990፣ 991፣ 987፣ 816 እንዲሁም በ011-1-26-43-59፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በእጅ ስልኮች የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን በመጠቀም ጥቆማ እንዲሰጥ ተጠይቋል፡፡

