አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ካርድ በመውሰድ ያሳየነውን ተሳትፎ ድምፅ በመስጠትም እናረጋግጣለን አሉ።
ወጣቶቹ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በወሰዱት ካርድ ድምፃቸውን በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በነገው እለት ድምፅ ለመስጠት በድሬዳዋ ያለውን ዝግጁነት በተመለከተ ኢዜአ የተለያዩ ወጣቶችን አነጋግሯል።
የዘንድሮው ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፉበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ያነሱት ወጣቶቹ፤ ካርድ በመውሰድ ያሳዩትን ተሳትፎ ድምፅ በመስጠትም የሚያረጋግጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቶቹ ኢድል ፋራህ፣ ሜላት አባተ እና ናስር መሐመድ፤ የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት በመገንባት የወደፊቷን ኢትዮጵያ ለማጽናት በሚደረገው ጥረት አሻራችንን ለማኖር ተዘጋጅተናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በተለይም የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን እንረዳለን በማለት ገልጸው፤ በድምፅ መሪዎችን መምረጥና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሀገርን ማጽናት የሁላችንም አደራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሌሎች አስተያየት ሰጭ ወጣቶች ረድኤት መኮንን፣ ጃሚ ዲኔ እና ኢድሪስ ሙሳ፤ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ለምርጫው ቀደም ብለው መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ነገ በሚካሄደው ምርጫ በወሰዱት ካርድ ድምፃቸውን በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

