አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 4 ሺህ 97 ተንቀሳቃሽ እና ተቀማጭ ታዛቢዎችን በሁሉም ክልሎች ለማሰማራት ዝግጅት ተጠናቅቋል አለ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ፡፡
ህብረቱ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ባለከው መግለጫ÷ የኢትዮጵያ ሲቪል ምርጫ ትዝብት የእውቅና ፈቃድ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሚከናወነው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ በምርጫ ትዝብት ለመሳተፍ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ ቆይቷል።
በዚህም መሰረት ግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ህብረቱ ከ101 አባል ድርጅቶች የመለመላቸውን 4 ሺህ 97 የአጭር ጊዜ ታዛቢዎችን ለማሰማራት ዝግጅቱን ጨርሷል።
ከተሰማሩት የአጭር ግዜ ታዛቢዎች ውስጥ 3 ሺህ 301 ተቀማጭ ታዛቢዎች ሲሆኑ 1 ሺህ 60 ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ከነዚህ ውስጥ 2 ሺህ 746 (67 በመቶ) ወንድ፣ 1 ሺህ 351 (33 በመቶ) ሴት ሲሆኑ፤ ከእነዚህ መካከል 197 (4 ነጥብ 8) አካል ጉዳተኞች እንደሆኑ ገልጿል፡፡
የኅብረቱ የአጭር ግዜ ታዛቢዎችን ለትዝብት ከማሰማራቱ በፊት የትዝብት ሥራቸውን በገለልተኝነት፣ በነጻነት፣ ሕግና መርሆችን ባካበረ መንገድ እንዲተገብሩ የሚያስችል ስልጠና ሰጥቷል።
ኅብረት ለምርጫ የትዝብት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሠራር በመዘርጋት 80 የሰለጠኑ ዳታ ሰብሳቢዎች ያሉበት የዳታ ማዕከል አቋቁሟል።
በዚህም ታዛቢዎች የሚያቀርቡት መረጃ በተዘረጋው ዘመናዊ የሪፖርት ማቅረቢያ ሥርዓት ላይ ብቻ ተመስርቶ የሚሰበሰብ ይሆናል።
ኅብረቱ የትዝብት ሂደቱን በተመለከተ የእኩለ ቀን ሪፖርት እና የመጀመሪያ ደረጃ መግለጫ የሚሰጥ መሆኑንም አመላክቷል፡፡
#ኢትዮጵያ #ኢትዮጵያትመርጣለች #በምርጫብቻ #ፋናዲጂታል #Election #fanadigital #Ethiopia #Ethiopiavotes #Democracy #fanatelevision

