አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በ7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አህመድ ያሲን ድምፃቸውን ከሰጡ በኋላ በሰጡት አስተያየት÷ ያለፉት 27 ዓመታት ስንጨፈጨፍበት የነበረው ቦታ ዛሬ የምርጫ ጣቢያ ሆኖ በነፃነት መርጠንበታል ብለዋል።
በምርጫው ሂደት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው አብሮ የመሥራት እና የመቀናጀት መንፈስ የሚደነቅ መሆኑንም ምክትል ሊቀመንበሩ ጠቅሰዋል።
ሕዝቡ ያለምንም ማስገደድ እና ጫና የወደደውን እና ያሻውን ፓርቲ በነፃነት እየመረጠ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡
ፓርቲው ለረጅም ጊዜ በምርጫ ሳይሳተፍ መቆየቱን አስታውሰው÷ ዛሬ ለዚህ ታሪካዊ ቀን የበቁት በሀገሪቱ በመጣው አጠቃላይ ለውጥ ምክንያት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በተያያዘ የኅብረት ለዴሞክራሲ እና ለነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ መሀመድ አድን ባስተላለፉት መልዕክት እስካሁን ያለው የምርጫ ሂደት እጅግ ሰላማዊ እና አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
መራጩ ሕዝብም ይህንን ዳግም የማይገኝ ታሪካዊ ዕድል በመጠቀም በነቂስ ወጥቶ ድምፁን እንዲሰጥ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

