Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሰርጋቸው ዕለት ድምጽ የሰጡ ሙሽሮች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሙሽሮቹ በሆሳዕና ከተማ በሌሞ 01 የምርጫ ክልል በሄጦ ቀበሌ መስኪድ ሰፈር ምርጫ ጣቢያ 07 በመገኘት ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

ሙሽራ ሰላሙ ዳንኤል እንደገለጸው፤ የሰርጋቸው ዕለትና የምርጫው ቀን በመገጣጠሙ አጋጣሚውን ተጠቅመው ድምጽ ሰጥተዋል።

በሰርጋችን ዕለት በርካታ ፕሮግራሞች ቢኖሩብንም ምርጫው የእኛንም ሆነ የሀገራችንን የቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወሰንበት በመሆኑ ድምጻችን ሰጥተናል ብሏል።

ዕለቱ የሰርጋችን ቀን ቢሆንም ኢትዮጵያን ማስቀደም ስላለብን ድምጻችንን ሰጥተናል ያለው ሙሽራው ለኢትዮጵያም ሆነ ለእኛ ይበጃል ያልነውን መርጠናል ሲል አክሏል።

የሚሰጡት ድምጽ የእነሱንም ሆነ የሀገሪቱን የቀጣይ እጣ ፈንታ የተሻለ ከማድረግ አኳያ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት የደስታ ፕሮግራማቸውን አቋርጠው ድምፃቸውን ለመስጠት በምርጫ ጣቢያው መገኘታቸውን ተናግሯል።

ሙሽሪት ብሩክ ገብሬ በበኩሏ፤ የሰርግ ቀናቸው ከምርጫ ቀኑ ጋር በመገጣጠሙ በምርጫው ድምፅ በመስጠት አሻራቸውን ለማኖር ወስነው እንደነበር አስታውሳለች።

የድምፅ መስጫው ቀን ከሰርጋቸው ቀን ጋር አንድ በመሆኑ የተለየ ደስታ እንደፈጠረባት መናገሯን ኢዜአ ዘግቧል።

በምርጫው በመሳተፍ ይሆነኛል ለምትለው ፓርቲ ድምጿን መስጠት በመቻሏ ከራሷ አልፎ የሀገሯን እጣ ፈንታ እንድትወስን እድል የፈጠረላት በመሆኑ ድርብ ደስታን እንደፈጠረላትም ገልፃለች።

#ኢትዮጵያ #ኢትዮጵያእየመረጠችነው #በምርጫብቻ #ፋናዲጂታል #Election #fanadigital #Ethiopia #Ethiopiavotes #Democracy #fanatelevision.

Exit mobile version