Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊት የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ)በህገወጥ የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊት የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች ከነመሳሪያቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎችን በኢትዮ ቴሌኮም ሳተላይት ኔትወርክ በኩል ማለፍ ሲገባቸው ፤ህገወጥ የቴሎኮም መሳሪያዎችን ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው ወደ አገር ውስጥ በማስገባትና ዓለምአቀፍ ጥሪዎችን በመጥለፍ በራሳቸው መሰመሮች ለደንበኞች እያቀረቡ ህገወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ናቸው በቁጥጥር ሰር የዋሉት፡፡

ግለሰቦቹም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከኢንፎርሜሽን መረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ጋር በቅንጅት በተደረገ ጥናትና ክትትል ነው ከተለያዩ ሕገወጥ መሳሪያዎች ጋር ሊያዙ የቻሉት ተብሏል፡፡

ለዚህ ህገወጥ ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 11 ጌትዌይ (ሲምቦክስ)፣ 26 ቲፕሊንክ፣ 1 ሺህ 339 ሲም ካርዶች፣ 20 ፍላሽ ዲሰክ፣ 11 ላፕቶፕ እና ሌሎች ህገወጥ የቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያመለከተው መግለጫው ህገወጥ ድርጊቱ ኢትዮ ቴሌኮምን በአመት እስከ 137 ሚልየን ብር እንደሚያሳጣው ተጠቁሟል፡፡

ህብረተሰቡም እንደዚህ አይነት ህግወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ሲመለከተ አካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉም ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጥሪ አቅርቧል፡፡

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከኢንፎርሜሽን መረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ጋር ከዚህ በፊት በቅንጅት ባደረጋቸው ተከታታይ ኦፕሬሽኖች መሰል የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊቶችን ማስቀረቱ ይታወሳል፡፡

Exit mobile version