አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የፋና 80 አማካሪ ሁለገቡ የጥበብ ሰው አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ባጋጠመው ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
አርቲስት ኪዳኔ ግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሲሆን÷ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ አማኑኤል ቤተክርስቲያን ይፈጸማል።
አርቲስቱ በሙያው ባገለገለበት ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ቤተሰቦቹ፣ ጎደኞቹ፣ የሙያ አጋሮቹና አድናቂዎቹ በተገኙበት የሽኝትና የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
በ1958 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ከእናቱ ከወ/ሮ ብዙነሽ ጓንጉል እና ከአባቱ ከአቶ ምስጋናው ደርኬሮ የተወለደው አርቲስት ኪዳኔ የጥበብ ጉዞን የጀመረው በቀበሌ ኪነትና በከፍተኛ ኪነት ውስጥ ሲሆን÷ ከዚያም በአዲስ አበባ ቴአትርና ባሕል አዳራሽ በ1977 ዓ.ም በውዝዋዜ ሙያ መቀጠር ችሏል፡፡
በዚያም ከተወዛዋዥነት ወደ ረዳት አሰልጣኝነት ከፍ በማለት ከ1983 እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ በረዳት አሰልጣኝነት ሙያ ያገለገለ ሲሆን÷ ከ1991 እስከ 1992 ዓ.ም ደግሞ በቋሚ አሰልጣኝነት በርካታ ባለሙያዎችን በክህሎት እና በሥነምግባር አሰልጥኖ ለውዝዋዜ ሙያ እድገት የበኩሉን ድርሻ አበርክቷል፡፡
በእውቀት፣ በልምድና በፈጠራ አንቱታን ማትረፍ የቻለው አርቲስት ኪዳኔ÷ የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በመቀላቀል ከ1992 እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ በዋና አሰልጣኝነትና በኬሮጋራፈርነት በርካታ በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዘፍ የነሱ መድረኮች ላይ የቀረቡ የውዝዋዜ ስራዎችን በማዘጋጀት፣ በማማከርና በመምራት ከሰው ልብና አዕምሮ የማይጠፉ ደማቅ ኪነጥበባዊ ስራዎችን ሰርቷል፡፡
በአንጋፋው ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ከ15 ዓመታት በላይ በአሰልጣኝነት ሲሰራ ከቆየ በኋላ ከ2007 እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ወደ ቀድሞ የሙያ ቤቱ የአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አደራሽ ተዘዋውሮ በአሰልጣኝነት እና በኬሮግራፈርነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
አሰልጣኝ፣ ኬሮግራፈር እና የውዝዋዜ አማካሪ አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ከተወዛዋዠነት፣ አሰልጣኝነት፣ አዘጋጅነትና አማካሪነት ባሻገር በድምጻዊነትና በቴአትር እና ፊልም ተዋናይነትም በመሳተፍ ሁለገብ ከያኒነቱን ያስመሰከረ ድንቅ ጥበበኛ ነበር፡፡
ለተለያዩ የቴሌቪዥን ዝግጅቶችና የበዓል ፕሮግራሞች ላይ ባቀረባቸው የጥበብ ስራዎች ድምቀት የነበረው አርቲስት ኪዳኔ በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ፋና 80 የውዝዋዜ እና የዳንስ ተሰጥኦ ውድድር ላይ በአማካሪነት በመስራት ሙያዊ አስተዋጽዖ አበርክቷል።
ሁለገቡ ከያኒ አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ህይወቱ እስካለፈበት ግንቦት 23/2018 ዓ.ም ድረስ ወደ አንጋፋው ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተዘዋውሮ በሙያው ሀገሩን እና ወገኑን በታማኝነትና በትጋት አገልግሏል።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው በፋና 80 የውዝዋዜ እና የዳንስ የተሰጥኦ ውድድር ላይ በአማካሪነት በመስራት ላበረከተው ሙያዊ አስተዋፅኦ እያመሰገነ ለቤተሰቦቹ፣ ለሙያ አጋሮቹ እና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል።

