Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቶማስ ፓርቴይ ዓለም ዋንጫ በሚሳተፈው የጋና ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ተካተተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀድሞው የአርሰናል አማካይ ቶማስ ፓርቴይ በዓለም ዋንጫ በሚሳተፈው የጋና ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ተካትቷል፡፡

ከፈረንጆቹ 2020 እስከ 2022 በአራት ሴቶች የጾታዊ ጥቃት ክስ የቀረበበት ቶማስ ፓርቴይ የቀረቡበት ሁሉም ክሶች ሐሰት መሆናቸውን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

የ32 ዓመቱ ተጫዋች አሁን ላይ ለስፔን ላሊጋው ክለብ ቪያ ሪያል እየተጫወተ ሲሆን÷ የቀድሞ ብቃቱ ከድቶት ተስተውሏል፡፡

የጋና ኤፍኤ ፕሬዚዳንት ኩርት ኦክራኩ ቶማስ ምክትል አምበላችን ነው፤ እሱ በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ አማካዮች አንዱ ነው በማለት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜው ከጎኑ እንቆማለን ብለዋል።

የጋና ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ካርሎስ ኪሮሽ ቶማስ ፓርቴይን ለዓለም ዋንጫ ዝግጅት ብሎም ከዌልስ ጋር ላለባቸው የወዳጅነት ጨዋታ የቡድኑ አካል አድርገውታል፡፡

የስፓርታክ ሞስኮው ተከላካይ አሌክሳንደር ጂኩ እንዲሁም የቶተንሃሙ ሞሀመድ ኩዱስ በጉዳት ከብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውጪ የሆኑ ተጨዋቾች ናቸው፡፡

የማንቼስተር ሲቲው አንቶኢን ሴሜኞ፣ የኮቨንተሪ ሲቲው አጥቂ ብራንዶን ቶማስ አሳንቴ እንዲሁም የሌስተር ሲቲ ተጫዋቾች የሆኑት ጆርዳን አዩ እና አብዱል ፋታው ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ጋና የምድቧን የመጀመሪያ ጨዋታ በካናዳ ቶሮንቶ ከፓናማ ጋር ትጫወታለች፡፡

በአቤል ነዋይ

Exit mobile version