Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፌዴራል ፖሊስ የታጠቃቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለምርጫው ውጤታማነት…

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የታጠቃቸው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ውጤታማነት በማስጠበቅ ረገድ ገንቢ ሚና ተጫውቷል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በትናንትናው ዕለት የተካሄደ ሲሆን÷ በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ስር የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በዛሬው ዕለት ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶችን በመለጠፍ ዜጎች እየተመለከቱ ይገኛል።

የድምጽ አሰጣጥ ሂደትም ፍጹም ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና ገለልተኝነቱን ጠብቆ እንዲካሄድ የፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ስራ ሰርቷል።

የፌዴራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ ማስፋፊያ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደምሴ ይልማ እንደገለጹት÷ ተቋሙ በምርጫው ወቅት ዜጎች በነጻነት ድምጻቸውን የሚሰጡበትን ሂደት ለማገዝ ሰፊ ዝግጅት አድርጓል።

በተለይም በአዳዲስና ፈጣን እድገት ላይ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ከነባሮቹ የቴክኖሎጂ መሰረተልማቶች ጋር በማቀናጀት፣ የፖሊስ ሰራዊት ስምሪት እና የምርጫ ጣቢያዎችን እንቅስቃሴ እያንዳንዱን በቀጥታ ለመከታተል መቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም በየአካባቢው የሚታየውን የፀጥታ ሁኔታና የምርጫ ድባብ አመራሩ ከኮማንድ ኮንትሮል ማዕከል ሲከታተል መቆየቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሁሉም የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በሰራው ስራ የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ መከናወኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version