Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢራን በኩዌት እና ባህሬን ላይ የድሮን ጥቃት ፈፀመች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአሜሪካ ጋር ድርድር እያደረገች የምትገኘው ኢራን በኩዌት አውሮፕላን ማረፊያ እና ባህሬን በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ የድሮን ጥቃት ፈፅማለች፡፡

ኢራን በኩዌት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማሪፊያ ላይ በፈፀመችው የድሮን ጥቃት በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው ሲገለፅ፤ በረራም ተቋርጧል ነው የተባለው፡፡

የኩዌት የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ሳኡድ አብዱልአዚዝ አል-ኦታይቢ÷ ኢራን በአውሮፕላን ማረፊያው የመንገደኞች ማረፊያ ህንፃ ላይ በፈፀመችው ጥቃት በሰዎች እና በህንፃው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል፡፡

በተመሳሳይ ኢራን በባህሬን በሚገኘው የአሜሪካ አምስተኛ መርከቦች ዋና መስሪያ ቤት ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈፀሟን የኢራን አብዮታዊ ዘብ አስታውቋል፡፡

ጥቃቱን ተከትሎ አብዮታዊ ዘቡ በሰጠው መግለጫ፤ በኢራን ለሚሰነዘር ማንኛውም አይነት ጥቃት አፀፋችን የከፋ እና የማያዳግም ነው ሲል አስጠንቅቋል፡፡

አሜሪካ በበኩሏ “ራስን መከላከል” ስትል በገለፀችው ዘመቻ በሆርሙዝ ሰርጥ አቅራቢያ በምትገኘው የኢራኗ ቃሺም ደሴት ላይ ጥቃት ፈፅማለች፡፡

የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድር ከተጀመረ በኋላ ከፍተኛ በተባለው የአፀፋ ምልልስ ኢራን እና አሜሪካ ምሽቱን በርካታ ጥቃቶችን ሲሰነዛዘሩ አድረዋል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቴህራን እና ዋሽንግተን እየተካሄደ ያለው ድርድር መቀጠሉን ገልጸው÷ የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲራዘም ለኢራን ተደራዳሪዎች ጥያቄ መቅረቡን ገልፀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢራን አሜሪካ ላቀረበችው የተኩስ አቁም ቀነ ገደብ ማራዘም ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም መባሉን አይቲቪ እና ቢቢሲ ዘግበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version